ኢትዮጵያን የምስራቅ አፍሪካ የታዳሽ ኃይል ምንጭ ለማድረግ እየተሰራ ነው

Published by corporate communication on

በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ትኩረት በተሰጠው የኢነርጂ ዘርፍ ኢትዮጵያን የምስራቅ አፍሪካ የታዳሽ ኃይል ምንጭ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ዛሬ በሂልተን ሆቴል በገንዘብ ሚኒስቴርና በመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ተገምግሟል፡፡

በዚህ ወቅት የገንዘብ ሚኒሰትሩ  አቶ አህመድ ሺዴ እንደገለጹት፥ መንግስት ለኃይል ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት የሰጠ በመሆኑ በጥንቃቄ የሚከታተለውና የሚመራው ዘርፍ ነው፡፡

በኃይል ማመንጨትና ማሰራጨት ዘርፍ ያለው የሪፎርም ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትና የዘርፉ የፕሮጀክት አመራርና አፈጻጸም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡

በሁለቱም ተቋማት በኩል ከደንበኞች ያልተሰበሰበ ገንዘብ በጊዜ እንዲሰበሰብ በተለይም ወደ ጎረቤት ሀገሮች ኤክስፖርት ከተደረገው  ኃይል ያልተሰበሰበውን ገንዘብ ተከታትሎ ገቢ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

የኃይል ብክነትንና መቆራረጥን መቆጣጠር፣ ወጪ ቅነሳን ተግባራዊ ማድረግ፣ በክልሎች ተግባራዊ እየተደረገ ያለውን የዘርፉን ያልተማከለ አስተዳደር አጠናክሮ መቀጠል አስፈላጊ መሆኑን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

የገንዘብ ሚኒስቴር  ከልማት አጋሮች ጋር በመተባበር አስፈላጊውን ድጋፍ ለተቋማቱ እንደሚሰጥ ማረጋገጣቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

19 − 8 =