ኢትዮጵያን እናልብስ በሚል መሪ ቃል የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና ተጠሪ ተቋማቱ ሠራተኞች የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብርን በይፋ ጀምረዋል

የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማቱ የሦስተኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በፊንፊኔ ልዩ ዞን በረህ ወረዳ ሲሬ ጉዮ ቀበሌ ማህበር ለገዳዲ ግድብ አካባቢ በዛሬው እለት በይፋ ተጀምሯል።
መርሃ ግብሩን ያስጀመሩት የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እንደተናገሩት በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ያለው የአንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአፈር መሸርሸር ምክንያት ደለል ወደ ኃይል ማመንጫ ግድቦች እንዳይገባ በማድረግ ግድቦች ኃይል ለማመንጨት የሚያስፈልጋቸውን ውሃ በአግባቡ እንዲይዙ ያደርጋል፡፡
እየተካሄደ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሃገራችንን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም እና ስነ ምህዳርን ለመጠበቅ እንዲሁም የውሃ አጠቃቀምን በማሻሻል ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወትም አብራርተዋል፡፡
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና የተጠሪ ተቋማት ሠራተኞች ባለፉት ሁለት ዓመታት በተካሄዱ መርሃ ግብሮች ላይ ለአካባቢው ስነ- ምህዳር ተስማሚ የሆኑ ችግኞችን በመትከል በንቃት ሲሳተፉ እንደነበር አስታውሰው በዛሬው መርሃ ግብር በስምንት ሄክታር መሬት ላይ የተለያየ ዝርያ ያላቸው 10 ሺህ ሀገር በቀል ችግኞች መተከላቸውን ገልፀዋል፡፡
በቀጣይም በወንዝ ተፋሰሶች እና ሐይቆች አካባቢ ትኩረት በማድረግ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡
እንደሚኒስትሩ ገለፃ ችግኝ መትከል ብቻ ለውጥ ስለማያመጣ የተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁ ለማድረግም ትኩረት ተሰጥቶት ይሰራል፡፡
ሁሉም ስነ -ምህዳርን መንከባከብ አስፈላጊ መሆኑን ተገንዝቦ እንደ ሃገር የታሰበውን ለማሳካት በቀጣይ የአረንጓዴ አሻራ ስራን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
በኦሮሚያ ክልል የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ፍቃዱ ቱሉ በበኩላቸው በዛሬው ዕለት የተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለአዲስ አበባ ከተማ የተጣራ ውሃ በማቅረብ ላይ የሚገኘውን የለገዳዲ ግድብን ከደለል ለመከላከል ያግዛል ብለዋል።
አካባቢው ለአዲስ አበባ ቅርብ በመሆኑ ከተማዋን ከአየር ንብረት መዛባት ለመጠበቅ እንደሚያስችልም ጠቁመዋል።
የውሃ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት የጀመሩትን መልካም ተሞክሮ ሌሎች የፌዴራልና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተቋማት በአካባቢው ላይ በመምጣት እንዲያስቀጥሉና የአረንጓዴ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ጥሪ አቅርበዋል።
ለዚህም ልዩ ዞኑና ወረዳ አስተዳደሩ መሬት ከማዘጋጀት ጀምሮ ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አሸብር ባልቻ በበኩላቸው መርሃ ግብሩ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን ከደለል ለመከላከልና ጣቢያዎቹ በሙሉ አቅማቸው ኃይል እንዲያመነጩ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል።
በማመንጫ ጣቢያዎች አካባቢ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ የአረንጓዴ አሻራ ስራውን ለማከናወን እቅድ መያዙንም ተናግረዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ አነሳሸነት በተጀመረው በዚህ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአራት ዓመት ውስጥ 20 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል እቅድ ተይዞ እየተሰራ ሲሆን ባለፉት ሁለት ዓመታትም ለመትከል ከታቀደው በላይ ችግኞችን መትከል ተችሏል፡፡
“ኑ ኢትዮጵያን እናልብሳት” በሚል መሪ ቃል ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይም በሃገር አቀፍ ጀረጃ 6 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል እቅድ ተይዞ በመሰራት ላይ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ በሃገር ውስጥ ከምታከናውነው የአረንጓዴ አሻራ ስራ በተጨማሪ በተያዘው ክረምት ለጎረቤት ሃገራት አንድ ቢሊዮን ችግኞችን በማቅረብ የአረንጓዴ አሻራን ወደ ቀጠናው ለማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቶት በመሰራት ላይ ይገኛል።
በውሃ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስቴር ፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና በቪተን ኢቪደንስ ኢንተርናሽናል ማህበር አስተባባሪነት በተዘጋጀው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብ ላይ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አሸብር ባልቻ፣ የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ም/አስተዳዳሪ አቶ ፍቃዱ ቱሉን ፧ ጨምሮ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና ተጠሪ ተቋማት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የዞኑ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሥራ መሪዎች እና ሠራተኞች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡
0 Comments