አገልግሎት የማይሰጡ ንብረቶችን በማስወገድ ከ33 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት የማይሰጡ የተለያዩ ንብረቶችን በማስወገድ በ2012 በጀት ዓመት 33 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን የተቋሙ ንብረት አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው ስራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ ዳዲ እንደገለፁት ገቢው የተገኘው አገልግሎት የማይሰጡ ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶች፣ አልሙኒየም፣ መዳብ፣ የተለያዩ የዕቃ ማሸጊያ ጣውላዎች፣ ያገለገሉ የተሸከርካሪ ጎማዎች እና የተለያዩ ተሽከርካሪዎችን በማስወገድ ነው፡፡
በበጀት ዓመቱ አገልግሎት የማይሰጡ ንብረቶችን በማስወገድ 20 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 33 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
ይህም ከእቅዱ የ66 በመቶ ብልጫ እንዳለው እና ከ2011 በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ149 በመቶ ብልጫ እንዳሳየ ነው አቶ ታደሰ የገለጹት፡፡
ቀደም ሲል ያገለገሉ ንብረቶች ሽያጭ ሲከናወን የነበረው በመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ሲሆን የመንግስት ንብረት አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 9/2003 መሰረት በማድረግ ተቋሙ ባወጣው የንብረት አስተዳደር እና አወጋገድ መመሪያ መሰረት የንብረት ማስወገድ ስራው በተቋሙ እየተከናወነ እንደሚገኝ ስራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡
እንደ አቶ ታደሰ ገለፃ የስራ ክፍሎች እንዲወገድላቸው የሚያቀርቡት ጥያቄ በተቋቋመው የንብረት አስወጋጅ ኮሚቴ ታይቶ ንብረቶቹ በሚገኙበት አካባቢ ተመሳሳይ ንብረቶች የሚሸጡበትን ዋጋና የመንግስት ንብረት ማስወገድ አጄንሲ ያወጣውን መነሻ የጨረታ ዋጋ ታሳቢ በማድረግ በግልጽ ጨረታ ሽያጩ ይከናወናል፡፡
በአሁኑ ወቅትም አገልግሎት የማይሰጡ ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶች፣ አልሙኒየም፣ ጣውላዎች፣ አሮጌ የቤት ክዳን ቆርቆሮዎች፣ ባህርዛፍ፣ በርሜሎች፣ ያገለገሉ ጎማዎች እና ተሸከርካሪዎችን ለማስወገድ እየተሰራ መሆኑን አቶ ታደሰ ተናግረዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ለነበረዉ የገቢ አሰባሰብ እድገት የተቋሙ አመራር ጥንካሬ እና በአሁኑ ወቅት ንብረት የማስወገድ ስልጣን ለተቋሙ መሰጠቱ በምክንያትነት ተጠቅሷል፡፡
በሌላ በኩል ንብረቶች በህጋዊ መንገድ በጨረታ በሚወገድበት ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች ንብረቶቹ እንዳይነሱ የመከልከል፣ ወደ ጣቢያዎች ግቢ በህገወጥ መንገድ በመግባት ቋሚ ንብረቶችን የመውሰድና ቤት የመስራት እንዲሁም የሰራተኞች መኖሪያ ቤትን ለመንጠቅ የሚደረጉ ሙከራዎች ቢሮው እያጋጠሙት ያሉ ተግዳሮቶች መሆናቸውን አቶ ታደሰ ጠቁመዋል፡፡
ችግሮችን ለመፍታትም ከክልል የፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት በመሰራት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
0 Comments