አገልግሎት ከማይሰጡ ንብረቶች ከ72 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

Published by corporate communication on

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በ2013 በጀት ዓመት አገልግሎት የማይሰጡ የተለያዩ ንብረቶችን በማስወገድ 72 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን የተቋሙ የንብረት አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ሥራ አስኪያጅ አቶ አበበ ጉዲሳ እንዳስታወቁት ገቢው የተገኘው አገልግሎት የማይሰጡ ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶች፣ መዳብ፣ አልሙኒየም፣ ዘይት የመጣባቸው በርሜሎች፣ ሽቦዎች፣ የተሸከርካሪ ጎማዎች፣ የዕቃ ማሸጊያ ጣውላዎች እና የመሳሰሉትን ንብረቶች በማስወገድ ነው፡፡

በበጀት ዓመቱ አገልግሎት የማይሰጡ ንብረቶችን በማስወገድ 40 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 72 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

ይህም ከእቅዱ የ32 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ወይም የ80 ነጥብ 2 በመቶ ብልጫ እንዳለው እና ከ2012 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ41 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ወይም  138 በመቶ ብልጫ እንዳለው ነው አቶ አበበ የገለጹት፡፡

አገልግሎት የማይሰጡ ንብረቶችን የማስወገዱ ሥራ የመንግስት ንብረት አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 9/2003 መሰረት በማድረግ ተቋሙ ባወጣው የንብረት ማስወገድ መመሪያ መሰረት በግልጽ ጨረታ መከናወኑን እንደነበር አቶ አበበ ተናግረዋል፡፡

የስራ ክፍሎች አገልግሎት የማይሰጡ ንብረቶች እንዲወገድላቸው በሚያቀርቡት ጥያቄ መሰረት በተቋቋመው የንብረት አስወጋጅ ኮሚቴ ታይቶ በግልጽ ጨረታ ሽያጩ ሲከናወን እንደነበርም ተገልጿል፡፡

በበጀት ዓመቱ ለነበረዉ የገቢ አሰባሰብ እድገት እንዲወገዱ የተጠየቁ ንብረቶች መጠን ከፍተኛ መሆን፣ በማስወገድ ሂደቱ ውስጥ በኮሚቴነት የተሳተፉ ኃላፊዎች እና ሰራተኞች ጥንካሬ እና ለስራው ያደረጉት ትብብርና በተቋሙ እየተፈጠረ ባለው የንብረት ማስወገድ ስራ ግንዛቤ ማደጉ በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡

አገልግሎት የማይሰጡ ንብረቶችን ህጋዊ በሆነ መንገድ በጨረታ ለማስወገድ በሚሰራበት ወቅት አንዳንድ የፕሮጀክት እና የኦፕሬሽን ኃላፊዎች ለስራው ቀና ትብብር አለማድረጋቸው እና በሶስተኛ ወገን የሚወገዱ ንብረቶችን ያለ ምንም ሕጋዊ ማስረጃ ለመውሰድ ፍላጎት መታየታቸው በበጀት ዓመቱ ቢሮው ያጋጠሙት ተግዳሮቶች መሆናቸውን አቶ አበበ ጠቁመዋል፡፡

እንደ አቶ አበበ ገለፃ በቴክኖሎጂ የታገዘ የንብረት ማደራጀት ስራው ሲጠናቀቅ፤ የተቋሙን ንብረቶች መረጃ በየጊዜው ወቅታዊ ለማድረግ፣ ለመቆጣጠር፣ በአግባቡ ለመጠቀም የሚያግዙ የተለያዩ የአሰራር ዘዴዎችን ለመተግበር በሂደት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

በተቋሙ የንብረት አያያዝ እና አስተዳደር ላይ የሚታየውን ክፍተት በዘላቂነት ለመሙላት ዘመናዊ የዕቃ ግምጃ ቤት ለመገንባት፣ የአይ. ኤፍ. አር. ኤስ፣ የንብረት ዋጋ ክለሳ እንዲሁም የኢ. አር. ፒ (Enterprise Resource planning) ሲስተም የመዘርጋት ሥራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

sixteen − 15 =