አይ ኤፍ አር ኤስ ለመተግበር እየተሰራ ያለው ስራ በመጠናቀቅ ላይ ነው

Published by corporate communication on

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ስርዓትን (International Financial Reporting Standard) ለመተግበር እየሰራ ያለውን ስራ በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን በተቋሙ የንብረት ዋጋ ክለሳና አይ ኤፍ አር ኤስ ትግበራ ፕሮጀክት መምሪያ አስታወቀ፡፡

የመምሪያው ስራ አስኪያጅ አቶ ይርጉ ኃይሉ እንዳስታወቁት ተቋሙ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ስርዓትን ለመተግበር ፌር ፋክስ እና ፒ ደብሊው ሲ (PWC) ከተሰኙ ሁለት ኩባንያዎች ጋር ስምምነት በማድረግ ወደ ስራ ገብቷል፡፡

በአሁኑ ሰዓትም የንብረት ቆጠራውን መረጃ የመሰብሰብና ወደ ገንዘብ የተመን የዋጋ ክለሳ ስራዉ ተጠናቋል፡፡

የ24 ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች፣ 129 ማከፋፈያ ጣቢያዎች፣ 36 ሺህ 210 የኃይል ተሸካሚ ምሶሶዎች፣ 9 መቶ 48 ተሸከርካሪዎችንና ማሽነሪዎች፣ 48 ሺህ የቤትና የቢሮ ዕቃዎችን እንዲሁም የ3 ሺህ 232 ህንፃዎች የዋጋ ትመና ስራ መከናወኑንም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

በቆጠራው የተካተቱ ንብረቶች ወደ ገንዘብ ሲተመኑ የተቋሙ ሀብት 382 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ አቶ ይርጉ አስታውቀዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለፃ የቆጠራና የትመና ስራው የተከናወነው እ.ኤ.አ. በ2016 እና ከዚህ በፊት አገልግሎት በመስጠት ላይ በነበሩት ንብረቶች ላይ በተካሄደ የአይ ኤፍ አር ኤስ ስራና የንብረት ክለሳ ስራ በመስራት ሲሆን የዋጋ ትመናው የገናሌ ዳዋ 3፣ የረጲ ከደረቅ ቆሻሻ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ እና በግንባታ ላይ ያሉትን ግዙፍ ፕሮጀክቶች አላጠቃለለም፡፡

ተቋሙ ፌር ፋክስ ከተሰኘ ኩባንያ ጋር ያሉትን ንብረቶች ለመቁጠርና የዋጋ ክለሳ ስራዎችን ለማከናወን የ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ስምምነት ተፈርሞ እንደነበር ያስታወሱት ስራ አስኪያጁ ኩባንያው በውሉ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች ስራውን ባለመፈፀሙ ተጨማሪ የጊዜ ማራዘሚያ ተሰጥቶት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለፃ ፌር ፋክስ በአሁኑ ወቅት ከማጠናቀቂያ ስራዎች በስተቀር የተሰጠውን ስራ በውሉ መሰረት ያከናወነ ሲሆን በተለያዩ ጊዜያት የተደረገለት የውል ማራዘሚያም ምንም ዓይነት የዋጋ ጭማሪ አልተደረገም፡፡

በተያያዘ ዜና ተቋሙ ከንብረት ቆጠራውና ዋጋ ክለሳ ስራው በተጓዳኝ ፒ ደብሊው ሲ ከተሰኘ ኩባንያ ጋር ስምምነት በማድረግ የIFRS የፋይናንሺያል ሪፖርት ስራዎች እያከናወነ ይገኛል፡፡

እስከ አሁንም እ.ኤ.አ. ከ2016 እስከ 2019 ያለውን የፋይናንስ ሪፖርት ማዘጋጀት መቻሉንና ከዚህ ውስጥም እ.ኤ.አ. ከ2016 እስከ 2018 ያለው የተቋሙ የመጀመሪያ የIFRS የፋይናንስ ሪፖርት ለሂሳብና ኦዲት ቦርድ ኮርፖሬሽን በማቅረብ የምርመራ ስራው እየተከናወነ እንደሆነ ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለፃ የኦዲት አገልግሎት ቦርድ የምርመራ ስራዉን ካጠናቀቀ በኋላ ተቋሙ ወደ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ስርዓት ትገበራ ይገባል፡፡

ከፒ ደብሊው ሲ ኩባንያ ጋር በ20 ወራት ውስጥ ስራዎችን አጠናቆ ለማስረከብ ስምምነት ተደርጎ የነበረ ቢሆንም ለተጨማሪ 5 ወራት ውል ተራዝሞለት ስራውን እያከናወነ መሆኑን አቶ ይርጉ አስረድተዋል፡፡

ከኩባንያው ካር የተደረገው ስምምነት የ2 ነጥብ 1 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ነው፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

1 + seventeen =