ታላቁ የኢትዮጵያ ግድብና የዩኒቨርስቲዎች ሚና ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሄደ

Published by corporate communication on

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመጪው ነሐሴ ወር መጨረሻ በሁለት ተርባይኖች ኃይል ለማመንጨት አስፈላጊ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ገለፁ፡፡

‘‘የዩኒቨርሲቲዎች ትብብርና የሳይንስ ዲፕሎማሲ ለዓባይ ዘለቄታዊ ልማትና የጋራ ተጠቃሚነት’’ በሚል ርዕሰ በጅማ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት በተካሄደ የውይይት መድረክ ላይ ኢንጂነር ክፍሌ እንደገለፁት ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት ለማከናውን አስፈላጊ ሥራዎች እየተሰሩ ነው፡፡

የግድቡ አጠቃላይ አፈፃፀምም 80 በመቶ መድረሱን ይፋ አድርገዋል፡፡

በዩኒቨርስቲው አዳራሽ ግንቦት 9 ቀን 2013 ዓ.ም የተካሄደውን ውይይት የከፈቱት የጅማ ዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ጀማል አባፊጣ በበኩላቸው እንደ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ያሉ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የጋራ አመለካከት ለመፍጠር፣ እውነታውን ለህብረተሰቡ ለማስዳት እና ግንዛቤ ለማሳደግ ከዩኒቨርስቲ ምሁራን ብዙ እንደሚጠበቅ ገልፀዋል፡፡ 

የዓባይ ወንዝ ለተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ሀብት በመሆኑ የጥርጣሬና ፉክክር መንስሄ ሊሆን አይገባም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የጋራ ተጠቃሚነት መርህን እተከተለች ቢሆንም ግብፅ የምታራምደውን እኔ ብቻ ልጠቀም የሚል ሃሳብ ለመመከት ምሁራን እና የዘርፉ ተመራማሪዎች ለህብረተሰቡ እና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ማስረዳት እንዳለባቸውም ነው የጠቆሙት፡፡

ሳይንስ ድንበር የለውም ያሉት ዶ/ር ጀማል ምሁራን በዓባይ ወንዝ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ላያ ያተኮሩ ጥናቶችን አጠናክሮ በመቀጠል በተለይና ግብፅና ሱዳን ያሉ ባለሙያዎችን በመጋበዝ መምከር፣ በጋራ መስራት እና የጋራ አቋም መያዝ እንደሚገባ  ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ የባለሙያዎች ቡድን አባል ፕ/ር ይልማ ስለሺ፤ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ  ‘‘ግብፅ እና ሱዳን ውሃ የለንም’’ የሚል የተሳሳተ ሃሳብ ለዓለም እያቀረቡ ቢሆንም ግብፅ 154 ትሪሊየን የከርሰ ምድር ውሃ እንዳላት ኢትዮጵያውያን ምሁራን ይህንን ለአለም ዓቀፍ ማህበረሰብ ማሳወቅ አለባቸው አስታውሰዋል ።

በምክክር መድረኩ ላይ የመንግስት ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ተወካዮች፣ ምሁራን እና የዘርፉ ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን ‘የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያለው ጠቀሜታ እና የምሁራን ሚና’’ በሚል ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል።

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

9 − one =