ተንሳፋፊ ሳርና የመለዋወጫ አቅርቦት እጥረት የጣቢያው ስጋት እየሆኑ ነው ተባለ

Published by corporate communication on

የበለስ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ተንሳፋፊ ሳርና የመለዋወጫ አቅርቦት ስራውን እያስተጓጎለበት መሆኑን የጣቢያው ኃላፊ ገለፁ፡፡

ኃላፊው አቶ ፍቃዱ ደምሴ እንደገለፁት ወደ ጣቢያው የውሃ መቀበያ እየተገመሰ የሚመጣው ተንሳፋፊ ሳር ለኃይል ማመንጫው የኦፕሬሽን ሥራ ከፍተኛ ስጋት እየሆነ ነው፡፡

ተንሳፋፊ ሳሩ ከሐምሌ 9-11 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ የኃይል ማመንጫ ጣቢያውን እስከማስቆም ደርሶ እንደነበረ የገለፁት ኃላፊው ባለፈው ዓመትም በተንሳፋፊ ሳሩ ምክንያት ከ10 ቀን በላይ ጣቢያው መቆሙን አስታውሰዋል፡፡

ጣቢያውን መልሶ ሥራ ለማስጀመር ኤክስካቬተር በመከራየትና ዋና በሚችሉ የጣቢያው ሠራተኞችን በመጠቀም የኃይል ማመንጫውን ውሃ መቀበያ የዘጋውን ተንሳፋፊው ሣር ለጊዜውም ቢሆን በማስወገድ ሥራ ማስጀመር መቻሉን አቶ ፍቃዱ ተናግረዋል፡፡

ጣቢያውን ከተንሳፋፊ ሳር ለመጠበቅ የሚያግዝ መከላከያ (Taff Boom) ያለው ቢሆንም በዘንድሮ ዓመት ከሃይቁ ዳር እየተገመሰ የሚመጣው የሳር ደሴት መጠኑ ከፍተኛ በመሆኑ ቀደም ሲል የተገጠመው መከላለያ ሊመልሰው አልቻለም፡፡

በመሆኑም በየጊዜው ወደ ኃይል ማመንጫው ለሚመጣው ተንሳፋፊ ሳር ዘላቂ መፍትሄ ካልተሰጠው በቀር ጣቢያውን እስከ መዘጋት ሊያደርሰው እንደሚችል አብራርተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በጊዜያዊነት ጀልባ በመከራየት ተቆርሶ የሚመጣውን የሳር ደሴት ለማስወገድ እየተሰራ እንደሚገኝ ኃላፊው ገልፀዋል፡፡

በመሆኑም ሳሩን ሊያወጣ የሚችል ኤክስካቬተርና ጀልባ በግዢ እንዲሟላ ኃላፊው ጠይቀዋል፡፡

ከዚህ በተጓዳኝ የበለስ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ እንደአብዛኛዎቹ ጣቢያዎች የመለዋወጫ አቅርቦት ችግር ያለበት ስለሆነ ችግሩን ለመፍታት ተቋሙ አፋጣኝ መፍትሔ ሊሰጥ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የበለስ ዘርፈ ብዙ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ለሀገሪቱ የኃይል አቅርቦት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

20 + 10 =