ተቋማዊ ለውጡን ለማስቀጠል የአፈፃፀም አመራር ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል ተባለ

Published by corporate communication on


በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተጀመረውን ተቋማዊ ለውጥ ሥር እንዲሰድ ለማድረግ የአፈፃፀም አመራር (performance management) ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ተገለፀ፡፡

ተቋሙ በአዲስ አበባ ውስጥ ለሚገኙ ማከፋፈያ ጣቢያ ሥራ አስኪያጆች በአፈፃፀም አመራር ስርዓትና በተቋሙ ስትራቴጅክ እቅድ ላይ ያተኮረ ሥልጠና ህዳር 17 ቀን 2012 ዓ.ም መስጠት ጀምሯል፡፡

በተቋሙ የፐርፎረማንስና ሪዋርድ ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተማም አፍደል እንደገለጹት፤ ስልጠናው አመራሩ የተቋሙን ስትራቴጂ በመረዳት በየደረጃው ባሉ ሠራተኞች ማስተግበር እንዲችሉና ሠራተኞችም ስትራቴጂውን የዕለት ተዕለት ተግባራቸው እንዲያደርጉት ለማድረግ ያግዛል፡፡

የአፈፃፀም አመራር ስርዓት መዘርጋቱ እያንዳንዱ ሰራተኛ በአቀደውና በሠራው ልክ እንዲመዘን ለማድረግ እንደሚያግዝ አብራርተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በተቋሙ ውስጥ ወጥነት ያለው የአፈፃፀም አመራር ሥርዓት ባለመኖሩ ሰዋዊ ባህሪያቶች ብቻ ሲለኩ እንደነበር ያነሱት ሥራ አስኪያጁ በአሁኑ ሰዓት ወጥነት ያለው የአፈፃፀም አመራር ስርዓት ለመተግብረ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ተማም ገለፃ ስርዓቱ ሲዘረጋ የተሻለ ሥራ የሠሩ የሚበረታቱበትና ዝቅ ያሉት ደግሞ ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲመጡ ከማድረግ በተጨማሪ ተቋማዊ ባህል እንዲጎለብትና የተለያዩ የአስተዳደራዊ የለውጥ ሥራችን ለመተግበር ይጠቅማል፡፡

በየደረጃው የሚገኝ ሁሉም የተቋሙ ሰራተኛ በቀጣይ የሚመዘነው በአፈጻፀም አመራር ስርዓት በመሆኑ ለተግባራዊነቱ በየደረጃው ያለ የስራ መሪና ሠራተኛ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አቶ ተማም አስታዉቀዋል፡፡

በስልጠናው ወቅት ተሳታፊዎች በየስራ ክፍላቸው በአፈጻፀም አመራር ስርዓት ላይ የነበሩ ችግሮችን በማንሳት ውይይትና ልምድ የሚለዋወጡበት መንገድ ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በሥልጠናው ላይ 36 የሚሆኑ የስራ መሪዎች የተሳተፉ ሲሆን ይህን መሰል ሥልጠና ከዚህ በፊት ከደቡብ ምዕራብ ሪጅንና ከትራንስሚሽን ሰብስቴሽን ኦፕሬሽን የስራ ዘርፍ ለተውጣጡ ሠራተኞች ተሰጥቷል፡፡

በቀጣይም ስልጠናው ለሌሎች ክፍሎች እንደሚሰጥ ለማወቅ ተችሏል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

3 × 2 =