ተቋሙ የ25 ዓመት መሪ ዕቅድ እያዘጋጀ ነው

Published by corporate communication on

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የ25 ዓመት መሪ ዕቅድ እያዘጋጀ መሆኑን በተቋሙ የኮርፖሬት ፕላኒንግ ሥራ አስፈፃሚ አስታወቁ፡፡

ሥራ አስፈጻሚው አቶ አንዱዓለም ሲዓ እንዳስታወቁት ሀገሪቱ ዘመናዊ የኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመገንባት እያደረገችው ላለው ጥረት የኤሌክትሪክ ኃይል ቀድሞ መገኘት ስላለበት የኤሌክትሪክ ዘርፍ የ25 ዓመት መሪ ዕቅድ ማዘጋጀት አስፈልጓል፡፡

በዚህም ዕቅዱ የኤሌክትሪክ ኃይል ለሀገር ዕድገት ያለውን ድርሻ በሚያሳይ መልኩ መሪ ዕቅዱ እየተዘጋጀ ይገኛል ብለዋል፡፡

መሪ እቅዱ ከአሜሪካ መንግስት በተገኘ የ5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እርዳታ ደብሊው ኤስ ፒ (WSP) ከተሰኘ የእንግሊዝ አማካሪ ኩባንያ ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑንም አቶ አንዱአለም ገልጸዋል፡፡

ኩባንያው የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ በማጥናት ወደ ፊት ምን አይነት ፍጆታ ይኖራል?  የኤሌክትሪክ ኃይል በምን አይነት መልኩ ተደራሽ መሆን አለበት? የሚገነቡ ፕሮጀክቶች ምን ዓይነት አካባቢዊና ማህበራዊ ተፅዕኖ ይኖራቸዋል? እንዲሁም ምን ያህል ወጪ ያስፈልጋቸዋል የሚለውን ስራ እንደሚያከናውን ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል፡፡

እስካሁን ባለው ጊዜ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ዘርፍ ዕቅድ መጠናቀቁን የጠቆሙት ሥራ አስፈጻሚው በ2014 ዓ.ም መጀመሪያ የ25 ዓመቱን ዕቅድ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የሚዘጋጀው መሪ ዕቅድ ከ10 ዓመቱ የዘርፉ ዕቅድ ጋር በተናበበ መልኩ እንዲሄድ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑንም አቶ አንዱአለም ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት የነበረው የኃይል ማመንጨት ሥራ በውሃ ላይ ጥገኛ የነበረ መሆኑን ያነሱት አቶ አንዱአለም በተለያየ ጊዜ ድርቅ ሲከሰት የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ይስተዋል ነበር ብለዋል፡፡

የ25 ዓመቱ መሪ ዕቅድ የኤሌክትሪክ ማመንጨት ሥራው ከውሃ ጥገኝነት ተላቆ በሌሎች የኤሌክትሪክ ኃይል ምንጮች ላይ ትኩረት በማድረግ ከዚህ በፊት ሰያጋጥሙ ለነበሩ ችግሮች መፍትሔ ይዞ ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

four × 3 =