ተቋሙ የፕሮጀክቶችን ማማከርና የዲዛይን ዝግጅት አቅሙ እያደገ መጥቷል

Published by corporate communication on

የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮችንና የማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቶችን በራስ ኃይል የማማከር አቅሙ እያደገ መምጣቱን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኢንጅነሪንግ ሥራ አስፈፃሚ አቶ አንዱዓለም ሲዓ ገለፁ፡፡

ሥራ አስፈፃሚው እንደገለፁት ተቋሙ ከ66 እስከ 500 ኪሎ ቮልት ያሉትን ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችንና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታ የማማከር ስራን ላለፉት 20 ዓመታት ሲያከናዉን ቆይቷል፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ አቅሙን በማሳደግ በአሁኑ ሰዓት የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን ግንባታ የማማከር ስራ በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አቶ አንዱዓለም ተናግረዋል፡፡

የኢንጅነሪንግ ቢሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በማመንጫ ጣቢያዎች ላይ በራስ ኃይል የማማከር ስራን ያከናወነው የአባ-ሳሙኤል የዉሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የዕድሳት ስራን ሲሰራ እንደነበር ያስታወሱት አቶ አንዱዓለም ተቋሙ በአሁኑ ሰዓት የአይሻ 2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን የማመከር ስራ በማከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

የኢንጂነሪንግ ቢሮው በአዲስ አበባ ቀላል ባቡርና ኢትዮ -ጂቡቲ የባቡር መስመር የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ፕሮጀክት እንዲሁም የታላቁ ህዳሴ ግድብ – ደዴሳ – ሆለታ ባለ 500 እና 400 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ ፕሮጀክት ጨምሮ እስከ አሁን በሃገሪቱ ተገንብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ በሚገኙት በርካታ የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቶች ላይ በማማከር ስራ ላይ እየተሳተፈ ነው ብለዋል፡፡

እንደ አቶ አንዱዓለም ገለፃ ተቋሙ በባለቤትነት ከሚያከናዉናቸው ፕሮጀክቶች በተጨማሪ በግል አልሚዎች የሚከናወኑ ፕሮጀክቶችን በማማከር ለተቋሙ ገቢ በማስገኘት ላይ ይገኛል፡፡

በአሁኑ ሰዓት ተቋሙ ከ25 በላይ የሚሆኑ ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር፣ ማከፋፈያ ጣቢያ እና ሌሎች ፕሮጀክቶችን በራስ ኃይል የማማከር ስራዎች በማከናወን ላይ እንደሚገኝም አቶ አንዱዓለም ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ አንዱዓለም ገለፃ ለአብዛኛው ፕሮጀክቶች አማካሪዎች የሚቀጠረው ከውጭ ሃገር በውጪ ምንዛሬ ነበር፡፡

ይሁንና ተቋሙ በራስ ኃይል የፕሮጀክቶችን የማማከር ስራ ማከናወኑ ለአማካሪ ቅጥር የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ በከፍተኛ ደረጃ ከማስቀረት በተጓዳኝ የዉጪ አማካሪ ለመቅጠር በሚደረገው ሂደት የሚፈጠረውን መጓተት በማስቀረት ፕሮጀክቶች በመርሃ ግብራቸው እንዲጀመሩ እና ጥራታቸውን ጠብቀው እንዲከናወኑ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል፡፡

የተቋሙ ኢንጅነሪንግ ቢሮ ከማማከር አገልግሎቱ የሚገኘዉን ልምድ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በሃገር ውስጥና ከሃገር ዉጪ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን በብቃት በማማከር ለተቋሙ ተጨማሪ ገቢ ለማምጣት ብሎም ለሃገር ተጨማሪ የዉጪ ምንዛሪ ምንጭ ለማስገኘት እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

268 ሰራተኞችን በመያዝ የፕሮጀክቶችን ግንባታ የማማከር ስራ በማከናወን ላይ የሚገኘው ቢሮው እንደ እንጦጦ እና አንድነት ፓርክ በመሳሰሉ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ የተለያዩ ሙያዊ ድጋፎችን በማድረግ የራሱን አሻራ ማሳረፍ ችሏል ነው ያሉት ሥራ አስፈፃሚው፡፡

ተቋሙ በራስ ኃይል ፕሮጀክቶችን ከማማከር በተጨማሪ የዲዛይን ስራዎችን ማከናወን በመቻሉ ለአዋሽ-ወልዲያ የባቡር መስመር የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ፕሮጀክት ዲዛይን ክለሳ ስራ ሊያወጣው የነበረውን 22 ሚሊዮን ዶላር ማዳን መቻሉን ነው ሰራ አስፈፃሚው የተናገሩት፡፡

በአሁኑ ሰዓትም ከ10 በላይ የሚሆኑ የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት ዲዛይን ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

ለስራው የሚያግዙ ዘመናዊ የቴክኖሎጅ መሳሪያዎች አቅርቦት እጥረት፣ የሰራተኛውን አቅም የሚያሳድጉ ስልጠናዎች አለመመቻቸት እና የባለሙያ እጥረት የማማከር ስራዎችን በተፈለገው መልኩ ለማከናወን ተግዳሮት መሆናቸውንና የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን ሥራ አስፈፃሚው ገልፀዋል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

14 + 17 =