ተቋሙ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን እና የፀረ ሙስና ቀን አከበረ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አመራርና ሰራተኞች “እኩልነትና ህብረ ብሄራዊ አንድነት ለጋራ ብልፅግና” በሚል መሪ ቃል 15ኛውን የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን አከበሩ፡፡
የተቋሙ የዋና ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙላት ገዛኸኝ በበዓሉ ላይ እንደተናገሩት የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ስናከብር በህዝቦች እኩልነት ላይ የተመሰረተ እውነተኛና ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት ዲሞክራሲ ለመገንባት ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የጀመረችውን የብልፅግና ጉዞ ለማገዝ ተቋማችን አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንዲኖር በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡
የዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የሚከበረው ከሃዲው የህወሓት ጁንታ ለመደምሰስ የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ባደረገው ታላቅ ተጋድሎ በተገኘው ድል ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ባሸነፈበት ወቅት በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
ሀገራዊ ሪፎርም ለጠንካራ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በሚል ርዕስ ነጻ፣ ገለልተኛና ብቃት ያላቸው ተቋማትን የመገንባት አስፈላጊነት የሚዳስስ ጥናታዊ ፅሁፍ ቀርቧል፡፡
በጥናታዊ ፅሁፉም የሀገራዊ ሪፎርሙ የትኩረት አቅጣጫዎች፣ የሀገረ መንግስትና ብሔረ መንግስት ግንባታ፣ የዲሞክራሲ ባህል እና የተቋማት ግንባታ እንዲሁም የፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ትስስር ዙሪያ ሰፊ ገለፃ ተደርጓል፡፡
ሀገራዊ ሪፎርሙ ለነፃ፣ ገለልተኛና ብቃት ያላቸው ተቋማት ግንባታ የሰጠው ትኩረት በሀገራችን ሕገ መንግስታዊ ፌዴራል ስርዓቱ ጤናማና ውጤታማ እንዲሆን እና ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ዲሞክራሲ እንዲሰፍን ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተጠቅሷል፡፡
ስለሆነም በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት ተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች ከየተቋማቸው ተልዕኮና ባህሪ አኳያ ለሪፎርሙ ውጤታማነት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል፡፡
በተያያዘ የተቋሙ አመራርና ሰራተኞች “የትውልድ ሥነ ምግባር ግንባታን በጠንካራ ዲሲፕሊን በመምራት ሌብነትን እና ብልሹ አሰራርን በመታገል የብልፅግና ጉዟችንን እናፋጥን” በሚል መሪ ቃል 16ኛው የፀረ ሙስና ቀን አክብረዋል፡፡
የተቋሙ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና መምሪያ ዳይሬክተር አቶ መርጋ ተረፈ በዓሉን ማክበር ያስፈለገው ሙስና በሚያስከትለው ጉዳት ላይ ግንዛቤ በመፍጠር የሙስና ወንጀልን በጋራ ለመከላከል ታስቦ ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም የተቋሙ አመራሮችና ሰራተኞች ራሳቸውን ከሙስናና ብልሹ አሰራር በማራቅ ተቋማዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡
0 Comments