ተቋሙ ከኃይል ኤክስፖርት ከ138 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት አቅዷል

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በተያዘው የበጀት ዓመት ከውጭ የኃይል ሽያጭ ከ1 መቶ 38 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት ማቀዱን በተቋሙ የማርኬቲንግና ቢዝነሰ ደቨሎፕመንት መምሪያ አስታወቀ፡፡
በመምሪያው የሽያጭና ደንበኞች አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ አቶ ሚኒሊክ ጌታሁን እንዳስታወቁት በተያዘው የበጀት ዓመት ለሱዳን፣ ለጅቡቲ እና ኬንያ ከ1 ነጥብ 63 ቢሊዮን ኪሎ ዋት ሰዓት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ 138 ነጥብ 25 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቀዷል፡፡
ገቢውን ለመሰብሰብ ለሱዳን 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ኪሎ ዋት ሠዓት ኤሌክትሪክ በማቅረብ 55 ነጥብ 48 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ለጅቡቲ 527 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኪሎ ዋት ሠዓት ኤሌክትሪክ በማቅረብ 34 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት መታሰቡን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
እስካሁን የኢነርጂ ኤክስፖርት ወዳልተጀመረበት ኬኒያ ወደ 695 ኪሎ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብና 48 ነጥብ 65 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ዕቅድ መያዙንም ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ በኩል የኢትዮ- ኬንያ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር በመጠናቀቁና የኬንያም ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ታሳቢ ተደርጎ ከጥር 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል ኤክስፖርት ለማድረግ እቅድ ተይዟል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለኬንያ 695 ሚሊዮን ኪሎ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ 48 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በኬንያ በኩል እየተገነባ ያለው የኢትዮ- ኬንያ የማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት ግንባታ ባለመጠናቀቁ ለኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ እንዳልተቻለ መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያ ከሦስቱ ሀገራት በተጨማሪ በቀጣይ ከሶማሌ ላንድ፣ ከታንዛኒያ እና ደቡብ ሱዳን እና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር የኤሌክትሪክ ኃይል ትስስር ለመፍጠር የሁለትዮሽ ግንኙነት በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡
0 Comments