ተቋሙ ኤች አይ ቪ እና ኮሮናን ለመከላከል የሚያግዝ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ

Published by corporate communication on

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ላይ የተሳተፉ ሠራተኞችን ከኤች አይቪ ኤድስ እና ከኮሮና ቫይረስ ለመከላከል ከዲኬቲ ኢትዮጵያና ከፌደራል ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ  ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ እንደተገለፀው ስምምነቱ በፕሮጀክቱ የተሳተፉ ሠራተኞችንና የአካባቢው ማህበረሰብን ከኤች አይ ቪ ኤድስና ከኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግና ሌሎች ቴክኒካል ስራዎችን ለማከናወን የሚያግዝ ነው፡፡

በስምምነቱ ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሰው ኃይል ስራ አስፈፃሚ አቶ አታላይ አበበ፣ በኢትዮጵያ የዲኬቲ ኢትዮጵያ ምክትል ዳይሬክተር ወ/ሮ ዳግማዊት ግርማይ እና የፌደራል ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጽጌሬዳ ክፍሌ ፊርማቸውን አኑረዋል፡፡

 በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ የሁሉም ዜጋ እንደሆነ በመረዳት ተቋማቱ እያደረጉት ያለውን ድጋፍ አቶ አታላይ አመስግነዋል፡፡

በህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ላይ የተሳተፉ ሠራተኞችን ደህንነትና ጤንነት ለመጠበቅ ተቋማቱ ከዚህ በፊት ሲያከናውኑ የነበረውን ድጋፍ ፕሮጀክቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡

ቫይረሱ በፕሮጀክቱ ሰራተኞች ላይ እንዳይሰራጭ ተቋሙ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም አቶ አታላይ አረጋግጠዋል፡፡

የፌደራል ኤች አይ ቪኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጽጌሬዳ ክፍሌ በበኩላቸው ኤች አይ ቪ ኤድስ በአሁኑ ሰዓት በሃገራችን የስርጭት አድማሱ እየተስፋፋ መሆኑን በመረዳት ለቫይረሱ ተጋላጭ በሆኑ ቦታዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የዲኬቲ ኢትዮጵያ ምክትል ዳይሬክተር ወ/ሮ ዳግማዊት ግርማይ እንደገለጹት ድርጅታቸው የግድቡ ፕሮጀክት ከተጀመረ ጀምሮ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ሲያደርግ የቆየውን የፋይናንስና ሌሎች ቴክኒካል ድጋፎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡

በዛሬው እለት የተካሄደው የድጋፍ ስምምነት ከ4 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ ሲሆን ይህም ለሦስት ዓመታት የሚቆይ ድጋፍ እንደሆነ በተቋሙ የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር አስተባባሪ አቶ መስፍን ደርሶ ተናግረዋል፡፡

ስምምነቱ በፕሮጀክቱ ላይ ለተሳተፉ ሠራተኞችና የአካባቢው ማህበረሰብ ስልጠና ለመስጠት፣ ሠራተኛው በትርፍ ጊዜው ወደ  አልባሌ ቦታ እንዳይሄድ በፕሮጀክቱ የመዝናኛ ቦታዎችን ለማዘጋጀት እና ሌሎች የንቅናቄ ስራዎችን ለማከናወን የሚውል መሆኑን ነው አቶ መስፍን የገለጹት፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

13 − 1 =