ተቋሙ በመሰረተ ልማቶቹ ላይ የደረሰበት ጉዳትና ኪሳራ ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ይገመታል

Published by corporate communication on

በአማራ እና በአፋር ክልሎች ህወኃት በፈፀመው ወረራ የወደሙ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶችን ለመጠገን የወጣው ወጪና በተቋሙ ላይ የደረሰው አጠቃላይ ኪሳራ 1 ነጥብ 64 ቢሊዮን እንደሚደርስ የኢትየጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡

በሁለቱ ክልሎች በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠንና ጉዳቱን ለመጠገን የተሰራውን ሥራ አስመልክቶ ተቋሙ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

በመግለጫው ላይ የተቋሙ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን እንደተናገሩት አሸባሪው የህወኃት ቡድን በአማራና በአፋር ክልሎች በፈፀመው ወረራ ምክንያት በክልሎቹ ከሚገኙት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ውስጥ 53 ነጥብ 3 በመቶ የሚሆነው ጉዳት ደርሶበታል፡፡

የደረሰው የኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማት ጉዳት የኮንዳክተር መበጠስ፣ የታወሮች መውደቅ፣ የተንቀሳቃሽ ማከፋፈያ ጣቢያ ተነቅሎ መወሰድ፣ የኦፕቲካል ግራውንድ ፋይበር መበጣጠስ እና የተሽከርካሪዎችና የቢሮ ፋሲሊቲዎች ዘረፋን እንደሚያጠቃልል ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

በደረሰው ጉዳት ከ14 ቀን እስከ 6 ወር የሚደርስ የኃይል አቅርቦት መቋረጡን እና ህብረተሰቡ ለከፍተኛ ችግር ተጋልጦ መቆየቱን ኃላፊው አስታውሰዋል፡፡

እንደ አቶ ሞገስ ገለፃ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን በመጠገን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦቱ በአስቸኳይ እንዲቀጥል ለማድረግ የወጣው የማቴሪያል ወጪ ብቻ ከ 29 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ነው፡፡

ሆኖም ጉዳቱን ሙሉ ለሙሉ በመልሶ ጥገና አስተካክሎ በአስተማማኝ ሁኔታ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ከ23 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የፋይናስ ወጪ እንደሚጠይቅ እና ይህም በቀጣይ ትኩረት ተደርጎበት እንደሚሰራ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

ከሐምሌ 26 ቀን 2013 ዓ.ም እስከ ታህሳስ 9 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ በደረሰው የመሰረተልማት ጉዳት 147 ነጥብ 19 ሚሊዮን ኪሎ ዋት ሰዓት ኤሌክትሪክ ሳይሸጥ የባከነ ሲሆን በገንዘብ ሲተመን 231 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር  ተቋሙን ለኪሳራ መዳረጉ በመግለጫው ተብራርቷል፡፡

ከወልዲያ ተነቅሎ የተወሰደው ተንቀሳቃሽ ማከፋፈያ ጣቢያ ከሁለት መቶ ሚሊየን ብር በላይ እንደሚገመት፣ በቢሮዎች፣ በማከፋፈያ ጣቢያዎችና በሰራተኞች መኖሪያ ቤቶች የደረሰው የንብረት ውድመትና ዝርፊያ ከ10 ሚሊየን ብር በላይ መሆኑንና ከሰሜን ምስራቅ ሪጅን የተወደሱት ተሸከርካሪዎች 12 ሚሊየን ብር እንደሚገመቱ ኃላፊው አንስተዋል፡፡

የወደሙ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶችን ለመጠገን የወጣው ወጪና በተቋሙ ላይ የደረሰው አጠቃላይ ኪሳራ 1 ነጥብ 64 ቢሊዮን እንደሚደርስ በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

ምንም እንኳን ተቋሙ በርካታ አካባቢዎችን ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ ማድረግ ቢችልም የወልቃይትና ሁመራ አካባቢዎች ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም  ጀምሮ ኤሌክትሪክ አለማግኘታቸውን በተመሳሳይም የላሊበላ፣ ሰቆጣና አካባቢው  ችግርም  አለመፈታቱን የተጠቆሙ  ዋና ደይሬክተሩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመነጋገር ችግሩን ለመቅረፍ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

በተቋሙ ላይ የደረሰው የ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ኪሳራ የማስተላለፊያ መስመሮችና የማከፋፈያ ጣቢያዎች የኦፕሬሽን ሥራዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት የሚያሳይ እንጂ የባህር ዳር – ወልዲያ – ኮምቦልቻ፣ የመቀሌ – ዳሎል – ሠመራ – አፍዴራ ፕሮጀክት  ጉዳቶች ያልተካተቱበት መሆኑን አቶ ሞገስ ገልፀዋል፡፡

በተጠቀሱት ፕሮጀክቶች ላይ የደረሰው የጉዳትመጠንና ኪሳራ ጥናቱ ሲጠናቀቅ ይፋ እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

two × two =