ተቋሙ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል

Published by corporate communication on

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተሰጠውን ሀገራዊ ተልዕኮ ለማሳካት ከሚያከናውናቸው ስራዎች ጎን ለጎን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ ማህበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡

ተቋሙ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ባጋጠሙ የተፈጥሮ አደጋዎች ችግር ለደረሰባቸው ወገኖች እንዲሁም መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ተወጥቷል፡፡

በበጀት ዓመቱ በጣና ሀይቅ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም ለመከላከል ሲሰራ ለነበረው የዘመቻ ስራ፣ በኦሞ እና በአዋሽ ወንዞች ሙላት ምክንያት ከቀያቸው ለተፈናቀሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ማቋቋሚያ እንዲሁም በተቋሙ የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ አማካኝነት ለተመረጠ የህጻናት ማሳደጊያ ተቋም የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፡፡

በኦሞ ወንዝ ሙላት ምክንያት የተነሳ አካባቢው በጎርፍ ሲጥለቀለቅ ለችግር ለተጋለጡት ወገኖች የገንዘብ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ ነዋሪዎቹ በጎርፍ እንዳይጎዱ ጀልባ በመከራየት የህይወት አድን ስራም አከናውኗል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽ/ቤት በሀገሪቱ እያከናወነ ለነበረው የገቢ ማሰባሰቢያ የንቅናቄ ስራ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ተችሏል፡፡ ተቋሙ በአዲስ አበባ ከተማ እየተደረገ ላለው የቤት ዕድሳትና ምገባ ፕሮግራም ላይ የበኩሉን አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡

በሀገሪቱ የሚከሰቱ የተለያዩ ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት እና በልማት ስራዎች ላይ የራሱን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያከናውነውን ስራ በተያዘው የ2014 በጀት ዓመት አጠናክሮ ይቀጥላል ተብሏል፡፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ማህበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት ሲከናወን የነበረው የድጋፍ ስራ ወጥነት ያልነበረው በመሆኑ በተያዘው የበጀት ዓመት ማህበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት የሚከናወኑ ስራዎችን ወጥነት ባለው መልኩ እንዲከናወኑ ለማድረግ የስፖንሰርሽፕ መመሪያ በመዘጋጀት ላይ ይገኛል፡፡

መመሪያው የሚመለከታቸው የስራ ክፍሎች አስተያየት ከሰጡበት በኋላ ለተቋሙ ከፍተኛ አመራር ቀርቦ ሲጸድቅ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል፡፡

በተጠናቀቀዉ የ2013 በጀት ዓመት ከገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ ሠራተኞችን በማስተባበር በጤና ተቋማት እየተስተዋለ ያለውን የደም እጥረት ለመቅረፍ የሚያግዝ የደም ልገሳ ፕሮግራም ተካሂዷል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

4 − 2 =