ተቋሙ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ለማዕከሉ እገዛ ማድረግ እንዳለበት ያምናል

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አሸብር ባልቻ ከመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መረጃ ማዕከል መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢኒያም በለጠ ጋር ተወያዩ፡፡
የማዕከሉ ሥራ አሰስኪያጅ አቶ ቢኒያም በለጠ ማዕከሉ አረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማንን ከጎዳና ላይ በማንሳት እየሰጠ ስላለው አገልግሎት ለዋና ስራ አስፈፃሚው ገለፃ አድርገውላቸዋል፡፡
ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ የሆነ ወጪ ማዕከሉ ያስጀመረውን ዘመናዊ ሆስፒታልና የአረጋውያን መኖሪያ ህንፃ ስለደረሰበት ደረጃም ገልፀውላቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እንደተቋም ለህንፃው ግንባታ የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ አቶ ቢኒያም ጠይቀዋል፡፡
የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አሸብር ባልቻ በበኩላቸው ማዕከሉ አረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማንን ከጎዳና በማንሳት እያከናወነ ያለው ተግባር ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው መሆኑን አንስተዋል፡፡
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ለማዕከሉ እንቅስቃሴ ፈተና ቢሆንም ያለምንም የውጭ እርዳታ አገልግሎቱ ሳይስተጓጎል መቀጠሉ የሚበረታታ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
ተቋሙም ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ለማዕከሉ እገዛ ማድረግ እንዳለበት ያምናል ብለዋል፡፡
በመሆኑም ማዕከሉ በምን ዓይነት መንገድ ቢታገዝ የተሻለ ይሆናል የሚለውን በመለየት ድጋፍ ለማድረግ ተቋሙ አማራጮችን እንደሚያጠና አቶ አሸብር ተናግረዋል፡፡
መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል በአዲስ አበባ ብቻ እስከ 4000 ሰዎችን ከጎዳና አንስቶ ድጋፍ በማድረግ ላይ የሚገኝ ሀገር በቀል የበጎ አድራጎት ማህበር ነው፡፡
0 Comments