ተቋሙ ለጥገና ስራ ያወጣ የነበረውን ወጪ የሚታደግ ሥራ እየተሰራ ነው

Published by corporate communication on

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለውሃ ፓምፕ ጥገና ያወጣ የነበረውን ተጨማሪ ወጪ መቀነስ መቻሉን የጢስ አባይ 1 እና 2 የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ አስታወቀ፡፡        

የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አቶ ደጀኔ ጉታ እንዳስታወቁት ኃይል ማመንጫዎች ሲጠቀሙባቸው የነበሩ የውሃ ፓምፖችን ለማስጠገን በጨረታ ለአንድ ፓምፕ 95 ሺህ ብር ዋጋ ቀርቦ ነበር፡፡    

ይሁን እንጂ የጢስ አባይ 2 የውሃ ኃይል ማመንጪ ጣቢያ  ሠራተኞች ባደረጉት ጥረት አንዱን ፓምፕ  ለመጠገን ሊወጣ በነበረው ገንዘብ መጠን አራቱን  መጠገን መቻሉን ተናግረዋል፡፡     

ጣቢያው አብዛኛውን ጊዜ ኃይል የሚያመነጨው ክረምት ላይ በመሆኑ የውሃ ፓምፕ  ችግር ይገጥመው እንደነበርና የመለዋወጫ አቅርቦትም በቀላሉ እንደማይገኝ አስታውሰዋል፡፡  

የተከናወነው የጥገና ሥራ  በጣቢያው የነበረውን የፓምፕ ጥያቄ ከመመለሱ  በተጨማሪ አራት ፓምፖችን በመጠገን ለበለስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን  ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል፡፡               

እንደ አቶ ደጀኔ ገለፃ በሰከንድ 250 ሺህ ሊትር  የተጠራቀመ ውሃ  የመሳብ አቅም ያለው ፓምፕ የጥገና ሥራም ተከናውናል፡፡ 

ይህንን ለማሰራት 150 ሺህ ብር ይጠይቅ እንደነበር የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ በጣቢያው ሠራተኞች ያለምንም ወጪ የጥገና ስራው ተጠናቋል ብለዋል፡፡     

የተከናወነው የጥገና ሥራ  የጣቢያውን የፓምፕ ችግር ከመቅረፍ  ባለፈ ፓምፖች የሚበላሹበትን ምክንያት በማወቅ ችግሩ  በድጋሚ እንዳይከስት ጥንቃቄ ለማድረግ ያግዛል ነው ያሉት፡፡  

በጣቢያው ከውሃ ፓምፖች የጥገና ሥራ በተጨማሪ የተርባይኑን አካላት የመጠገን ሥራ ማከናወን መቻሉን አቶ ደጀኔ ተናግረዋል፡፡

አቶ ደጀኔ እንዳሉት የጥገና ሥራው በጣቢያው ባለሙያዎች መሰራቱ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግሩ በተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ያሳያል፡፡

73 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው የጢስ አባይ 2 የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በ1993  ዓ.ም ነበር አገልግሎት መስጠት የጀመረው፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

seven − six =