ቤትና ንብረታቸው ለተቃጠለባቸው የተቋሙ ሠራተኞች የቁልፍ ርክክብ ተደረገ
በአዋሽ 2 እና 3 የውኃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ላይ በሰራተኞች መኖሪያ ቤት በደረሰ ድንገተኛ የእሳት አደጋ ቤትና ንበረታቸው ለተቃጠለባቸው ሠራተኞች የቁልፍ ርክክብ ተደረገ፡፡
ተቋሙ ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የቤት ግንባታ እና እድሳት ሥራ በማከናወን ሐምሌ 25 ቀን 2013 ዓ.ም ለተጎጂ ሠራተኞች የቤት ቁልፍ አስረክቧል።
በውጭ ሀገር ከሚኖሩ እና ከአካባቢው ማህበረሰብ የተሰበሰበውን የገንዘብ ድጋፍም ርክክብ ተፈጽሟል፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኃይል ማመንጫዎች ኦፕሬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ እያየሁ ሁንዴሳ እንደገለፁት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በአዋሽ 2 እና 3 ጣቢያዎች የጎርፍ መጥለቅለቅና የእሳት አደጋ ያደረሱትን ጉዳት በመቋቋም ሠራተኛውና ተቋሙ አፋጣኝ ምላሽ ሰጥተዋል።
ይህም በኦፕሬሽን ሥራዎች ላይ የጎላ ተፅዕኖ ሳያሳድር ችግሩ እንዲወገድ መደረጉ ሊደነቅ ይገባል ብለዋል።
ተቋሙ በ2014 በጀት ዓመት የያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ሁሉም የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት እንዳለባቸው ሥራ አስፈፃሚው አሳስበዋል፡፡
የአዋሽ 2 እና 3 የኃይል ማመንጫ ጣቢያ የሠራተኞች መኖሪያ ቤት ላይ መጋቢት 17 ቀን 2013 ዓ.ም እኩለ ለሊት ተከስቶ በነበረው የእሳት አደጋ 13 ቤቶች እንደተቃጠሉ መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በደረሰው አደጋም ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ሲወድም በሁለት ሰዎች ላይ የሞት አደጋ መድረሱ አይዘነጋም፡፡
0 Comments