ባለፉት ስድስት ወራት ከስድስት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማዳኑን ፍሊት ማኔጅመንት አስታወቀ

የተቋሙን ጋራዥ በሠው ኃይል እና በአጋዥ መሳሪያዎች አደራጅቶ ወደ ሥራ በመግባቱ ለተሽከርካሪ ጥገና ይውል የነበረ ከስድስት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማዳኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የፍሊት ማኔጅመንት ቢሮ አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የጋራዥ ሱፐርቫይዘር የሆኑት አቶ ጌቱ ዘላለም ባለፉት ስድስት ወራት በወር በአማካኝ ለ80 ተሽከርካሪዎች የጠቅላላ ጥገና አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኝ እና ባለፈው ህዳር ወር ብቻ ለ88 ያህል ተሽከርካሪዎች የጥገና አገልግሎት መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡
በሞይንኮ ጋራዥ ሙሉ ጥገና ለማድረግ ለአንድ ተሽከርካሪ እስከ 40 ሺህ ብር ክፍያ ይፈፀም እንደነበር ያስታወሱት አቶ ጌቱ በድርጅቱ ጋራዥ ግን ከ15 ሺህ ብር ባልበለጠ ወጪ ሙሉ የተሽከርካሪ ጥገና እያከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም የዘይትና የናፍጣ ፊልትሮን ለመቀየር ለሞይንኮ እስከ 18 ሺህ ይከፈል እንደነበር እና በተቋሙ ጋራዥ ግን በ3 ሺህ ብር ወጪ ማከናወን መቻሉንም ነው አቶ ጌቱ ያስረዱት፡፡
ተሽከርካሬዎች በተቋሙ ጋራዥ እንዲጠገኑ መደረጉ ከጊዜ ቁጠባ አኳያም ጉልህ ፋይዳ ያለው መሆንኑ የጠቆሙት አቶ ጌቱ ለአንድ ተሽከርካሪ ሙሉ የጥገና አገልግሎት ለመስጠት በሞይንኮ 2 ሳምንታት ይወስድ እንደነበርና በተቋሙ ጋራዥ ግን በአንድ ቀን ማጠናቀቅ እንደተቻለ አስታውቀዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ የኤሌክትሪክ፣የብሬክ ሲስተም፣የፍሬን ሸራ፣የመኪና ቦዲ፣ኤር ክሊነር እና ጠቅላላ የሞተር ጥገና አገልግሎቶች በጋራዡ እየተሠጡ መሆናቸውን ሱፐርቫይዘሩ አብራርተዋል፡፡
እነዚህን አገልግሎቶች ለመስጠት የሚያስችሉ የድሬኔጅ ጉድጓድ፣የመለዋወጫ ዕቃዎች፣የመፍቻ እና አነስተኛ ፓኮች ወይም ክሬኖች መሟላታቸውንም ነው አቶ ጌቱ የተናገሩት፡፡
በአሁኑ ጊዜ ጋራዡ 15 ሠራተኞች ያሉት መሆኑን፤ ለእነዚህም ሠራተኞች የዕውቀት እና የክህሎት ሥልጠና ለመስጠት ዝግጅት በመደረግ ላይ መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል፡፡
በፍሊት ማኔጅመንት የሠው ኃይል አስተዳደር ኃላፊ ወይዘሮ ቤተልሔም ዘውዱ ሠራተኞች በየዕለቱ የሚያከናውኗቸውን የተሽከርካሪ ጥገና ሥራዎች በመመዝገብና ሥራዎችን በመለካት በሥራ ውጤት ላይ የተመረኮዘ ማበረታቻና ጥቅማጥቅም ለመስጠት የሚያስችሉ ሰፊ ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው ብለዋል፡፡የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በጋራ የጋራዥ አገልግሎት ሲጠቀም የነበረ ሲሆን ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ የራሱን ጋራዥ እንደ አዲስ አቋቁሞ ጠቅላላ የተሽከርካሪ ጥገና አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
0 Comments