በ2012 በጀት ዓመት ከ15 ሺህ ጊጋ ዋት ሰዓት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ተችሏል

Published by corporate communication on

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በተጠናቀቀው የ2012 በጀት ዓመት 15,192 ነጥብ 11 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት መቻሉን የኃይል ማመንጫዎች ኦፕሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡

በጽ/ቤቱ የኃይል ማመንጫዎች ኦፕሬሽን ቴክኒካል ድጋፍ እና አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሰናይ ገ/ጊዮርጊስ እንዳስታወቁት በበጀት ዓመቱ 16,165 ነጥብ 48 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ዕቅድ ተይዞ 15,192 ነጥብ 11 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ተችሏል፡፡
አፈፃፀሙም የእቅዱ 94 በመቶ እንደተሳካ ያሳያል ነው ያሉት አቶ ሰናይ፡፡

እንደ አቶ ሰናይ ገለፃ በበጀት ዓመቱ የተጠበቀውን ያህል የኃይል ጥያቄ አለመቅረቡ እና የደንበኞች የሌሊት የኃይል አጠቃቀም ዝቅተኛ መሆኑ ለእቅዱ አለመሳካት ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡

የአይሻ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ወደ ኦፕሬሽን አለመግባቱ፣ የገናሌ ዳዋ 3ኛ የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በታቀደው ጊዜ ኃይል ማመንጨት አለመቻሉ እና ለጣቢያዎች የመለዋወጫ ዕቃ ባለመሟላቱ በጥገና ችግር የቆሙ የማመንጫ ዩኒቶች መኖራቸው ለእቅዱ አለመሳካት ተጨማሪ ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ በሃገሪቱ የኃይል እጥረት አለመከሰቱንም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ማመንጨት የተቻለው ኃይል ከ2011 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻፃፀር የ9.5 በመቶ ጭማሪ መኖሩን አቶ ሰናይ ገልፀዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት በሃገሪቱ 21 የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ጣና በለስ፣ ግልገል ግቤ I፣ ግቤ II፣ መልካ ዋከና፣ ጢስ ዓባይ II፣ ቆቃ ፣ አዋሽ 2፣ አመርቲ ነሼ እና ረጲ የደረቅ ቆሻሻ ጣቢያ ከታቀደላቸዉ በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት መቻላቸው ተጠቁሟል፡፡

አንዳንድ ጣቢያዎች ያመነጫሉ የተባለውን ኃይል በተለያዩ ምክንያቶች ማመንጨት ባይችሉም ጊቤ 3፣ ጣና በለስ እና ጊቤ 2 የኃይል ማመንጫ ጣቢያ በበጀት ዓመቱ ማመንጨት ከተቻለው ከፍተኛውን ኃይል ድርሻ ያበረከቱ ጣቢያዎች መሆናቸውን ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡

በጣቢያዎች ላይ መደበኛ የኦፕሬሽን ሥራ ሳይስተጓጎል ከጣቢያ እስከ ብሔራዊ የኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከል ድረስ የኦፕሬሽን ሥራውን ማዘመን የሚያስችሉ ተግባራት ሲከናወኑ እንደነበርም ተገልጿል፡፡

እንደ አቶ ሰናይ ገለፃ የኦፕሬሽን ስራዉን ሁልጊዜ አስተማማኝ ለማድረግ የዩኒቶች መደበኛ ዓመታዊና ልዩ ልዩ ጥገና በተጨማሪ የመሳሪያዎች ጥገና የብልሽት ቅድመ መከላከል የፍተሻ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡

በግድቦች ላይ አስተማማኝ ውሃ እንዲኖርና የውሃ እጥረት እንዳይከሰት ለማድረግ የዕለት ተዕለት የግድቦች የውሃ አስተዳደር ላይ ትኩረት ተሰጥቶት ሲሰራ እንደነበርና በዚህም ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን አቶ ሰናይ ተናግረዋል፡፡

በግድቦች አካባቢ ከሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር መልካም ግንኙነት እንዲኖር ለማድረግም በተለያየ ጊዜ የሚያነሷቸውን የተለያዩ የልማት ጥያቄዎችን የሚመልሱ የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡

በ2013 በጀት ዓመት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ደንበኞች አገልግሎት የሚውል 17,307 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማምረት እቅድ መያዙን ከጀኔሬሽን ኦፕሬሽን ስራ አስፈፃሚ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡

በበጀት ዓመቱ የጣቢያዎችን ዩኒቶች ሥራ ሊያስቆሙ የሚችሉ የመለዋወጫ ዕቃዎች አቅርቦት ላይ እና የጣቢያዎችን የኦፕሬሽን፣ ጥገናና ፍተሻ ሥራዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራም ተጠቁሟል፡፡

ነሐሴ 08 ቀን 2012 ዓ.ም.

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

nine + 6 =