በፕሮጀክቱ ንብረቶች ላይ እየተፈፀመ ያለው ስርቆት ተቋሙን ለተጨማሪ ወጪ ዳርጎታል

የኢትዮ- ኬንያ ባለ 500 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት ተደጋጋሚ የስርቆት ወንጀሎች እየተፈፀሙበት እንደሚገኝ የኢትዮ – ኬንያ የኃይል ማስተላለፊያ መስመርና ኮንቨርተር ጣቢያ ፕሮጀክት የግንባታ አስተባባሪ ገለፁ፡፡
አስተባባሪው አቶ ሰይፉ ፈይሳ እንደገለፁት በኢትዮጵያ በኩል የሚገነባው የ433 ኪሎ ሜትር የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል፡፡
ይሁን እንጅ በወላይታ ዞን አንዳንድ አካባቢዎች በማስተላለፊያ መስመሩ ሽቦዎች እና የምሰሶ ብረቶች ላይ በተደጋጋሚ የስርቆት ወንጀሎች እየተፈፀመበት ይገኛል ብለዋል፡፡
ይህም ተቋሙን ለተጨማሪ ወጪ በመዳረግ ከ34 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራም እንዳደረሰበት ነው ያስታወቁት፡፡
ኪሳራው የደረሰው በስርቆቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰበትን የማስተላለፊያ መስመሩን አካላት በአዲስ ለመተካትና ለመቀየር፣ እንዲሁም ለመበየድ፣ ለዕቃ ግዥ እና ለምሶሶ (Tower) ቅየራ ተጨማሪ ወጪ በመውጣቱ ነው፡፡
የማስተላለፊያ መስመሩ 994 ምሶሶች ያሉት ሲሆን በተፈፀመው ስርቆት ጉዳት ከደረሰባቸው ምሶሶዎች መካከል አንዱን ሙሉ በሙሉ መቀየሩን አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡
እንደርሳቸው ገለፃ እየተፈፀመ ያለው የስርቆት ወንጀል ተቋሙን ለተጨማሪ ወጪ ከመዳረጉም በላይ የማስተላለፊያ መስመሩን የፍተሻ ስራ በተያዘለት መርሃ ግብር ለማከናወን እንቅፋት ሆኗል፡፡
በአሁኑ ወቅት በዝርፊያው ጉዳት የደረሰባቸውን የማስተላለፊያ መስመር አካላት የመጠገን ስራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ የገለፁት አቶ ሰይፉ ጥገናውን በቅርቡ ለማጠናቅ እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
የጥገና ስራው ከተጠናቀቀ በኋላ የሙከራ ስራው በቅርቡ እንደሚጀመርም ነው አስተባባሪው የተናገሩት፡፡
በስርቆት ሲሳተፉ እጅ ከፈንጅ ተይዘው የነበሩ አካላት እና ሌሎች እጃቸው አለበት ተብሎ የተጠረጠሩ ጥቂት ግለሰቦች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ቢውሉም በአነስተኛ የገንዘብ ዋስትና እንዲለቀቁ መደረጉ ተገቢ እንዳልሆነ አስተባባሪው አንስተዋል፡፡
በተደጋጋሚ የሚስተዋለው የስርቆት ወንጀል ህጋዊ መፍትሄ እንዲያገኝ በየደረጃው ከሚገኙ የክልል የስራ ኃላፊዎች ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች መደረጉንና ችግሩን በደብዳቤ ጭምር የማሳወቅ ስራ ቢሰራም አሁንም መፍትሄ ማግኘት አለመቻሉን ጠቁመዋል፡፡
በስርቆት ወንጀል በሚሳተፉትና በተቀባዮቻቸው ላይ ተገቢ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ ካልተወሰደ የህዝብ ሀብት በሆነው የፕሮጀክቱ ንብረት ላይ ከፍ ያለ ጉዳት ሊያደርስ ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡
የኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ ልማቶች በከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚገነቡ በመሆናቸው ህብረተሰቡ የኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ ልማቶችን እንደራሱ ንብረት አድርጎ በመንከባከብና በመጠበቅ እንዲሁም ወንጀለኞችን ለፀጥታ አካላት በማጋለጥ በኩል ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል፡፡
የግንባታ ሰራው በ2008 ዓ. ም የተጀመረው የኢትዮ- ኬንያ ባለ 500 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት ከ185 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ በጀት ተይዞለት በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡
0 Comments