በጊቤ አንድ ኃይል ማመንጫ ግድብ ውሃው ሳይፈስ ስኬታማ ጥገና ተከናወነ

Published by corporate communication on

በጊቤ አንድ ኃይል ማመንጫ ግድብ ውሃው ሳይፈስ ከ18 ሜትር ጥልቀት በላይ ወደ ውሃ ውስጥ በመግባት ስኬታማ ጥገና መከናወኑን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አቶ ደሳለኝ ንጉሳ ገለጹ፡፡

ግድቡ ላይ 1.5 ሜትር ክበት ስንጥቅ በመኖሩ ግድቡ ውሃ የማስረግ ችግር ገጥሞት እንደነበር የገለፁት አቶ ደሳለኝ በዘመነ ቴክኖሎጂ አማካኝነት ውሃው ሳይፈስ ጥገናውን በማከናውን ችግሩን መቅረፍ ተችሏል ብለዋል፡፡

የቻይናው ሲጂጂሲ ኩባንያ የጥገና ሥራውን ያከናወነ ሲሆን ሌሎች ታዋቂ አለም አቀፍ ኩባንያዎች ውሃው ካልፈሰሰ መጠገን አንችልም ያሉትን ሲጂጂሲ ውሃው ሳይፈስ በመጠገን ለኃይል ማመንጫው በቂ የውሃ ክምችት እንዲኖር አስችሏል፡፡

በተጨማሪም የደለል ማስወገጃ እና መቆጣጠሪያ አሸንዳ በጉዳት ምክንያት አገልግሎት መስጠት አቋርጦ የነበረ ሲሆን ጥገና ተከናውኖለት ወደ ሥራ ለማስገባት የሙከራ እና የፍተሻ ሥራዎች የተከናወኑ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ደሳለኝ ገለፃ ለዚህ ጥገና አጋዥ የሆኑ የመቆጣጠሪያ ሰሌዳ እና የሞተር ፓምፕ ገጠማ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡

በጥገና ሥራው ላይ 31 ያህል ቻይናውያን የተሳተፉ ሲሆን የጣቢያው ሠራተኞችም በሥራው ላይ በመሳተፍ ጠቃሚ እውቀትና ክህሎት ማግኘታቸውንም ነው አቶ ደሳለኝ የገለፁት፡፡

የኃይል መቆጣጠሪያው ሥርዓት ተበላሽቶ ለቁጥጥር አስቸጋሪ እንደነበርና በራስ የሰው ኃይል ከኮምፒውተር ሞደፊኬሽን በመስራት አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጓል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ለመጠባበቂያ ጀነሬተር ማስቀመጫ የሚያገለግል ቤት መገንባቱንም ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል፡፡

ሥራ አስኪያጁ እንደተናገሩት ከጥገና ሥራዎች ባሻገር ለሠራተኞች ምቹ ከባቢ ለመፍጠር የመኖሪያና የቢሮ አካባቢዎችን የማፅዳትና የማስዋብ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡

ሠራተኞች በትርፍ ጊዜያቸው ራሳቸውን እንዲያዝናኑ የማዘወተሪያ ሥፍራዎችን የማደስና የዋይ ፋይ ኔትወርክ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም አቶ ደሳለኝ አብራርተዋል፡፡

በ1996 ዓ.ም ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የጊቤ አንድ የውሀ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ 184 ሜጋ ዋት ኢነርጂ የማመንጨት አቅም አለው፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

fifteen − 10 =