በደብረ ታቦር እና በበቆጂ አዳዲስ የማከፋፈያ ጣቢያዎች ሊገነቡ ነው

Published by corporate communication on

በአማራ ክልል በደብረ ታቦር ከተማ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል በበቆጂ ከተማ የማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታ ሊከናወን ነው፡፡

የደብረ ታቦር ባለ 230/33/15 ኪ.ቮ ማከፋፈያ ጣቢያ ከባህር ዳር – አላማጣ ከሚሄደው ባለ 230 ኪ.ቮ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተጠልፎ የሚገነባ ሲሆን የበቆጂ ማከፋፈያ ጣቢያ ከመልካ ዋከና – ቆቃ ከተዘረጋዉ ባለ 230 ኪ.ቮ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተጠልፎ የሚገነባ ነው፡፡

የማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ በከተሞቹና በአቅራቢያቸው ለሚገኙ ከተማዎች እና ወረዳዎች አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ  ያግዛሉ፡፡

የደብረ ታቦር ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክትን ለመገንባት 11 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንዲሁም  የበቆጂ ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክትን ለማከናወን 9 ነጥብ 9 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ይፈልጋል፡፡

የፕሮጀክቶች የግንባታ ስራ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የትራንስሚሽንና ሰብስቴሽን ኮንስትራክሽን የራስ ኃይል (own force) ቢሮ ይከናወናል፡፡

የፕሮጀክቶችን ግንባታ ለማከናወን የዕቃ አቅራቢ ግዢ ለማከናወን ከአበዳሪው ዓለም ባንክ ፍቃድ ተገኝቶ የጨረታ ሰነድ በመሸጥ ላይ ነው፡፡

በተመሳሳይ ዜና የጉራራ፣ ጎፋ እና መካኒሳ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታ እንዲሁም ሁለት የባለ 132 ኪ.ቮ ማስተላለፊያ መስመሮችን አቅም የማሳደግ ስራ ለማከናወን እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡

የፕሮጀክቶችን ስራ ለማከናወንም የአዋጭነት ጥናቱ የተጠናቀቀ ሲሆን ከአበዳሪው የአፍሪካ ልማት ባንክ ይሁንታ ከተገኘና ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ከተጠናቀቁ በኋላ የፕሮጀክቶቹ ግንባታ በተያዘው በጀት ዓመት ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

seven + 2 =