በዓመት 500 የኤሌክትሪክ ኃይል መሙያ ጣቢያዎችን ለመገንባት ዕቅድ ተይዟል

Published by corporate communication on

በዓመት 500 የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ኃይል መሙያ ጣቢያዎችን ለመገንባት ዕቅድ መያዙን ካርዲናል ኢንደስትሪያል ኃላፊቱ የተወሰነ የግል ማህበር አስታወቀ።የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና ካርዲናል ኢንደስትሪያል ኃላፊቱ የተወሰነ የግል ማህበር የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ኃይል መሙያ ጣቢያዎችን ለመገንባት የተስማሙበትን ሒደት አስመልክቶ በስካይ ላይት ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫው ላይ የካርዲናል ኢንደስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ሊሊያ ኃይሉ እንደገለፁት ድርጅቱ ከኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ኃይል መሙያ ጣቢያዎች ግንባታ ጎን ለጎን ዘመናዊ የፋይናንስ ሥርዓት ለመዘርጋት ታቅዷል።በአዲስ አበባና በአንዳንድ የክልል ከተሞች ለመገንባት የታቀዱት የኤሌክትሪክ ኃይል መሙያ ጣቢያዎች ብዛት በየዓመቱ እየጨመረ እንደሚሄድ ወ/ሮ ሊሊያ ተናግረዋል።በመጀመሪያው ዓመት ብቻ ለኤሌክትሪክ ኃይል መሙያ ጣቢያዎች ግንባታ እስከ 25 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚደረግም ነው ሥራ አስፈፃሚዋ የጠቆሙት።

በመግለጫው ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን እንደተናገሩት ተቋሙ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የሚያስፈልገውን ኃይል እና ለኃይል መሙያ ጣቢያዎቹ የሚያስፈልጉ መሠረተ ልማቶችን ለማቅረብ መዘጋጀቱን ገልፀዋል።የኃይል መሙያ ጣቢያዎቹ ግንባታዎቹ በዋናነት በሀገሪቱ  ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የኃይል ፍላጎት ለማርካት ያለመ መሆኑንም ነው ያብራሩት::የኃይል መሙያ ግንባታዎች የሚከናወኑት የተቋሙ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች በሚገኙባቸው ቦታዎች መሆኑ ለተደራሽነቱ ትልቅ ማሳያ ነውም ብለዋል።

የሚገነቡ የኃይል መሙያ ጣቢያዎች አሁን ባለው የኃይል አቅርቦት ላይ ተፅዕኖ ማሳረፍ እንዳይችሉ ራሳቸውን የቻሉ መስመሮች ከመገንባት ጀምሮ የተቋሙን የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች አቅም ሙሉ ለሙሉ ለመጠቀም የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን አቶ ሞገስ ተናግረዋል።አሁን ባለው ሁኔታ በዓመት እስከ 1ሺህ ጌጋ ዋት ሰዓት ኤሌክትሪክ ለኃይል መሙያ ጣቢያዎቹ ለማቅረብ የሚያስችል አቅም መኖሩን ተናግረዋል።ለተግባራዊ ለሚደረጉት የኃይል መሙያ ጣቢያዎ ኃይል በማቅረብ በዓመት እስከ አንድ ቢሊየን ብር ገቢ ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ሞገስ ጨምረው ጠቅሰዋል።

የኃይል መሙያ ጣቢያዎቹ ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ የታሰበው አገልግሎት እየሰጡ ከሚገኙ የማመንጫ ጣቢያዎች ነው ያሉት ዳይሬክተሩ  ወደፊት በግንባታ ላይ ያሉት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ በዕቅዱ ታሳቢ እንደሚደረጉም አስረድተዋል።መንግሥት ከውጭ በሚገቡም ሆነ በሀገር ውስጥ በሚመረቱ የኤሌክትሪክ የህዝብ ማመላለሻ፣ የቤት አውቶሞቢሎች እና የዕቃ መጫኛ ተሽከርካሪዎች ላይ የጉምሩክ ቀረጥ፣ የኤክሳይዝ ታክስ፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ እና የሱር ታክስ ማሻሻያዎች ማድረጉ ለኃይል መሙያ ጣቢያዎች መገንባት ዋነኛ ምክንያት ነው ተብሏል።መንግሥት በዓመት ለነዳጅ ፍጆታ ብቻ ከ3 እስከ 3 ነጥብ 5 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ወጪ የሚያደርግ ሲሆን በዓመት በአማካይ እስከ 4 ነጥብ 2 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ነዳጅ እንደሚቀርብም ነው መረጃዎች የሚያሳዩት።

“ከካርቦን ልቀት የፀዳ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል!”

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

7 − 2 =