በወልዲያ ከተማ የተጀመረው የከፍተኛ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ 48 በመቶ ደረሰ

Published by corporate communication on

በሰሜን  ወሎ ዞን  ወልድያ  ከተማ እየተገነባ የሚገኘው የወልዲያ ባለ 400 /230/33/15 ኪ.ቮ. የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት  አማካይ አፈጻጸም  48 በመቶ  መድረሱን  የባህርዳር-ኮምቦልቻ -ወልዲያ  ከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ እና ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት የሳይት ተቆጣጣሪ መሐንዲስ አቶ ሐብታሙ ተሾመ አስታወቁ፡፡

አቶ ሃብታሙ እንደገለፁት እስከ አሁን የኤሌክትሮ መካኒካልና የብረታ ብረት ተከላና ለኤሌክትሪክ ገመዶች ቀበራ የሚውል ግንባታ ፣ እንዲሁም  ሁለት የባለ 75 ሜጋ ቮልት አምፒር ትራንስፎርመር  ተከላና  ሁለት የባለ 500 ሜጋ ቮልት አምፒር  ትራንስፎርመር መትከያ  የመሰረት ግንባታ ተጠናቋል፡፡

የመቆጣጠሪያ ቤት፣ የሠራተኞች መኖሪያ ቤት፣ የጥበቃ ቤት፣ የስዊች ጊር ቤት ግንባታ፣ የፍሳሽ ማስወገጃ ግንባታ የማጠናቀቂያ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

በቀጣይም የጠጠር ንጣፍ፣ የውስጥ አጥር፣ የሲዊች ያርድ ግንባታ እና የኬብል ዝርጋታ ሥራዎች  ትኩረት ተሰጥቷቸው እንደሚከናወኑ መሐንዲሱ ጠቁመዋል፡፡

 የኤሌክትሮ  ሜካኒካል ዕቃዎችን የመገጣጠምና የብረታ ብረት ስራዎች  የተጠናቀቁ ሲሆን  በቀጣይ የስዊች ጊር  ስራዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው የሚሰሩ መሆናቸውን የሳይት መሐንዲሱ ተናግረዋል፡፡

ማከፋፈያ ጣቢያው  500 ሜጋ ቮልት አምፒር  አቅም ያላቸው ሁለት ትራንስፎርመሮች እና 150 ሜጋ ቮልት አምፒር  አቅም ያለቸው  ሁለት ባለ 75 ሜጋ ቮልት አምፒር ትራንስፎርመሮች ይኖሩታል፡፡

ለማከፋፈያው ጣቢያው የሚያስፈልጉት የተለያዩ  የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎች ከ 40 በመቶ በላይ ወደ ግንባታ ሥፍራው ተጓጉዘው  የደረሱ ሲሆን ቀሪዎቹም ተፈብርከው በቅርቡ ወደ ሀገር ቤት ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የፕሮጀክቱ   ሥራ አስኪያጅ  ወ/ሮ የትናየት  ይመር እንደተናገሩት የማከፋፈያ ጣቢያውን  ስራ  አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት  ከ913 ሚሊዮን ብር  በላይ ፋይናንስ  ተበጅቶለታል፡፡

ግንባታውን ሻንጋይ ኤሌክትሮ ግሩፕ  የተባለ የቻይና ኩባኒያ ሲያከናውን የአማካሪነት  ስራውን ደግሞ የኢትዮጵያ ኤሌከትሪክ ኃይል  እያከናወነ ይገኛል፡፡

የማከፋፈያ ጣቢያው ስምንት ባለ 33 ኪሎ ቮልት  እና  ስምንት ባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች  የሚኖሩት ሲሆን አማካይ  አፈጻጸሙ ከ ከ48 በመቶ በላይ ደርሷል፡፡

ማከፋፋያ ጣቢያው  ሲጠናቀቅ የወልዲያ  ኢንደስትሪ ፓርከ፣ የባቡር  ፕሮጀክቱ እና የወልዲያ  ከተማና የአካባቢው ን የኃይል ፍላጎት አቅርቦትን  ጥያቄ ከመመለሱም ባሻገር አስተማማኝ  ኃይል እንዲኖር በማድረግ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

seventeen − 7 =