በእሳት አደጋ ንብረታቸው ለወደመባቸው የኃይል ማመንጫው ሠራተኞች ድጋፍ ተደረገ

የአዋሽ 2 እና 3 የኃይል ማመንጫ ጣቢያ የሠራተኞች መኖሪያ ቤት ላይ መጋቢት 17 ቀን 2013 ዓ.ም እኩለ ለሊት ተከስቶ በነበረው የእሳት አደጋ ምክንያት ንብረታቸው ለወደመባቸው ሠራተኞች 882 ሺህ ብር ድጋፍ ተደረገ፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኃይል ማመንጫዎች ኦፕሬሽን ሥራ አስፈፃሚ አቶ እያዩ ሁንዴሳ ድጋፉን ለተጎጂ ሠራተኞች ባስረከቡበት ወቅት በጣቢያው የሠራተኞች መኖሪያ ላይ በደረሰው የእሳት አደጋ የሰው ህይወት በመጥፋቱ እና ንብረት በመውደሙ በእጅጉ ማዘናቸውን ገልፀዋል፡፡
ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም የተቋሙ ሥራ አመራር ኮሚቴ አዋቅሮ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል ያሉት አቶ እያዩ የተጎጂዎቹን ንብረት በተወሰነ መልኩ ለመተካት ጥረት ተደርጓልም ብለዋል፡፡
እንደ አቶ እያዩ ገለፃ ጉዳት የደረሰባቸውን መኖሪያ ቤቶች በአፋጣኝ መልሶ ለመጠገን 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ተመድቦ ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው፡፡
የዋና ሥራ አስፈፃሚ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙላት ገዛኸኝ በበኩላቸው የእሳት አደጋው በሰው እና በንብረት ላይ ጥፋት በማድረሱ በተቋሙ ሥራ አመራር ስም ሀዘናቸውን ገልፀው መሰል አደጋዎች እንዳይከሰቱም ጥንቃቄዎችን ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
አቶ ሙላት እንዳሉት ሠራተኛው የሚያጋጥሙትን ችግሮች ለመፍታት ተቋሙ ወደፊትም ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
የመሠረታዊ ሠራተኛ ማህበር ሊቀመንበር አቶ መኮንን ክፍሌ ደግሞ ማህበሩ ሠራተኞች አደጋ በገጠማቸው ወቅት ሁሉ ከተቋሙ ሥራ አመራር ጋር በመሆን የመፍትሔ አካል ሲሆን ቆይቷል ብለዋል፡፡
በአዋሽ 2 እና 3 የኃይል ማመንጫ ጣቢያ የሠራተኞች መኖሪያ ቤት ላይ በደረሰው የእሳት አደጋ የተጎዱትን ሠራተኞች ለማቋቋም የተደረገው አፋጣኝ ድጋፍ ምስጋና የሚያስቸረው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ሲወሰድ በነበረው የህግ ማስከበር ዘመቻ ወቅት ተቋሙ ከ600 እስከ 700 ለሚጠጉ ሠራተኞቹ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በመመደብ የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱንም አስታውሰዋል፡፡
በኃይል ማመንጫ ጣቢያው 19 ክፍሎች ባሉት የሠራተኞች መኖሪያ ብሎክ ላይ የደረሰው የእሳት አደጋ የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉና ከ 3 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙ የሚታወስ ነው፡፡
ተቋሙ ባደረገው እርዳታ ለእያንዳንዱ ተጎጂ እንደየጉዳቱ መጠን ከ13 ሺህ 5 መቶ እስከ 94 ሺህ ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡
0 Comments