በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች በስፋት ወደ ሥራ መግባታቸው ወጪን ለመቀነስ የጎላ ፋይዳ እንዳላቸው ተገለፀ

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በስፋት ወደ ሥራ መግባታቸው ለነዳጅ የሚወጣ ወጪን ከመቀነስ አኳያ ፋይዳቸው የጎላ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ፕላኒንግ ሥራ አስፈፃሚ አስታወቁ።ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የኃይል መሙያ ጣቢያ ለመገንባት በተዘጋጀው የማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት ላይ ሥራ አስፈፃሚው አቶ አንዱዓለም ሲኣ እንደገለፁት ህብረተሰቡ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ሲጠቀም እስከ 50 በመቶ የትራንስፖርት ወጪ ይቀንሳሉ።
ህብረተሰቡ በኃይል መሙያ ጣቢያዎች መስፋፋት የተነሳ የኃይል መቆራረጥ እንዳያጋጥመው ለመሙያ ጣቢያዎቹ ራሱን የቻለ መስመር ለመዘርጋት የሚያስችል በቂ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል።በኤሌክትሪክ ለሚሰሩ ተሽከርካሪዎች የኃይል መሙያ ጣቢያዎች ለመገንባት የፖሊሲና የህግ ማዕቀፍ ክፍተቶች እንዳያጋጥሙ ከወዲሁ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ተቋሙ ሙሉ ለሙሉ የአረንጓዴ ኢኮኖሚን የሚደግፍ ኃይል እያቀረበ እንደሚገኝ የጠቀሱት ሥራ አስፈፃሚው የካርቦን ልቀትን ለሚቀንሱ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አስተማማኝ ኃይል በማቅረብ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።እንደ አቶ አንዱዓለም ገለፃ በየጊዜው እያጋጠሙ ያሉ የኃይል መቆራረጦች በቂ ኃይል በግሪድ ቋት ውስጥ ባለመኖሩ ሳይሆን ለረጅም ዓመታት ማሻሻያ ሳይከናወንላቸው በቆዩ ያረጁ መስመሮችና ጣቢያዎች ምክንያት ነው።
አሁን ላይ ለሀገር ውስጥ እና ለጎረቤት ሀገራት እየቀረበ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን ከተቋሙ የማምረት አቅም 86 ከመቶ ብቻ መሆኑን ጠቅሰዋል።ተቋሙ የኃይል መሙያ ጣቢያዎችን በመገንባት መንግሥት የነዳጅ ፍጆታን ለመቀነስ የጀመረውን አበረታች ጅማሮ እንደሚያግዝም ነው ሥራ አስፈፃሚው የተናገሩት።ኢትዮጵያ ከውሃ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት በአፍሪካ ቀዳሚ ሀገር ስትሆን ግዙፍ የሆነ ግሪድ ከማስተዳደር አንፃር ከደቡብ አፍሪካ እና ግብፅ ቀጥላ በሦስተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ አቶ አንዱዓለም ጠቅሰዋል።
“ከካርቦን ልቀት የፀዳ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል!”
0 Comments