በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የካይዘን ትግበራ የመግባቢያ ሰነድ ተፈረመ

Published by corporate communication on

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት ጋር በትናትናው ዕለት የካይዘን ትግበራ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ፡፡

የመግባቢያ ሰነዱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አሸብር ባልቻ እና የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ተወካይ አቶ አስናቀ ጉዲሳ ተፈራርመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አሸብር ባልቻ በፊርማ ሥነ – ሥርዓቱ ላይ ተቋሙ ከ381 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት አጠቃላይ ሀብት እንዳለው ገልፀው ይህን ሀብት በአግባቡ ለመጠበቅ እና ለመጠቀም የካይዘን ትግበራ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡

የተቋሙን የሥራ ብቃት እና አፈጻጸም መዘመንና ማደግ ሀገሪቱ በምታካሄደው ሁለተናዊ  ዕድገት ላይ የሚጫወተውን ሚና የላቀ እንደሚያደርገው ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሰው ኃይል ሥራ አስፈጻሚ አቶ አታላይ አበበ በበኩላቸው ተቋሙ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት እና በተወሰኑ ቦታዎች በተካሄደው የካይዘን ትግበራ ድርጅቱን ወጪ ቆጣቢ በማድረግ ውጤታማና አበረታች ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ተቋሙ ባሉት 189 ማከፋፈያ ጠቢያዎች እና በ22 ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ላይ የካይዘን ፍልስፍና ትግበራን ለማስፋፋት እና ለመተግበር ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አቶ አታላይ ጠቁመዋል፡፡

የሚከናወኑትን የካይዘን ሥራዎች ለመምራት እና ለመተግበር የማኔጅመንቱን ቁርጠኝነት ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲቱት የዋና ዳይሬክተር ተወካይ አቶ አስናቀ ጉዲሳ እንደተናገሩት ካይዘን ማለት ጥራትና ምርታማነትን በቀጣይነት በማሻሻል ውጤታማ መሆን ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ኢንስቲቱ የተቋሙን ሠራተኞች በማሰልጠን እና ትግበራው ላይ በመገኘት የማመከር እና ድጋፍ በመስጠት ትግበራው ዘላቂነት እንዲኖረው ክትትል እና ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከፍተኛ ሃብት ከሚንቀሳቀስባቸው የሃገሪቱ ግዙፍ ተቋማት መካከል አንዱ እንደመሆኑ በትንሽ የካይዘን ሥራ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት እንደሚቻል አቶ አስናቀ ጠቁመዋል ፡፡

የፊርማ ሥነ-ስርዓቱ አሁን በይፋ ይካሄድ እንጂ ካለፉት ሶስት እና አራት ወራት አንስቶ ለሚመለካታቸው የተቋሙ ሠራተኞች ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

ባለፈው አንድ ወር ደግሞ በኮተቤ የንብረት ማከማቻ መጋዘን የትግበራ ሥራ ተጀምሯል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

8 − five =