በአባ ወረዳ አዲስ ባለ132/33 ኪ.ቮ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ሊገነባ ነው

Published by corporate communication on

በደቡብ ክልል ዳውሮ ዞን በአባ ወረዳ በ48 ሚሊዮን ብር ወጪ አዲስ ባለ 132/33 ኪ.ቮ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ሊገነባ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ሪጅን ሰብስቴሽንና ትራንስሚሽን ኦፕሬሽንና ጥገና ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ገዛኽኝ እንደገለፁት 1998 ዓ.ም. ተገንብቶ አገልግሎት  ሲሰጥ የቆየው የአባ ባለ 132/33 ኪ.ቮ. ማከፋፈያ ጣቢያ በ2012 ዓ.ም. በደረሰበት የመሬት መሸራተት የተነሳ አገልግሎት አቋርጧል፡፡

በመሆኑም ችግር የገጠመውን ማከፋፈያ ጣቢያ በአዲስ ባለ132/33 ኪ.ቮ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ለመተካት መወሰኑን ተናግረዋል፡፡

አካባቢው ኃይል እንዳያጣ አደጋው በደረሰበት ወቅት ተቀሳቃሽ (የሞባይል) የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ በጊዜያዊነት መተከሉን ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል፡፡

ተንቀሳቀሽ ማከፋፈያ ጣቢያው ባሉት 3 ባለ 33 ኪ.ቮ. ወጪ መስመሮች ለዳወሮ እና ለኮንታ ዞኖች ኃይል እየሰጠ ይገኛል ፡፡

የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው የሚገኝበት ቦታ የኦሞ ሸለቆ ውስጥ የሚገኝበት በመሆኑ ተደጋጋሚ የመሬት መሸራተት የሚከሰትበት አስቸጋሪ ቦታ ነው ፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም በተደረገው የአፈር ጥናት ከነባሩ ማከፋፈያ ጣቢያ  በ18 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ልዩ ስሙ ቦሪቃ በሚባል አለታማ ቦታ ላይ አዲስ ማከፋፈያ ለመገንባት የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ዳሬክተሩ አብራርተዋል፡፡

የግንባታ ሥራው በተቋሙ የራስ ኃይል በሁለት ዓመት ያልቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

አባ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ከአዲስ አበባ በ451 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

18 − eight =