በትግራይ ክልል በተካሔደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ከ240 ሚሊዬን ብር በላይ የሚገመት የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ደርሷል

Published by corporate communication on

በትግራይ ክልል በተካሔደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ወቅት ከ240 ሚሊዬን ብር በላይ የሚገመት የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት መድረሱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ ፡፡

የተቋሙ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮነን እንደገለፁት በህግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት በርካታ መሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ 

የሰሜን ሪጅን በተከዜ እና አሸጎዳ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙትን ሁለት ስዊችያርዶች ጨምሮ  17 የሚሆኑ የኃይል ማፋፈያ ጣቢያዎች እንዳሉት የጠቆሙት አቶ ሞገስ ከነዚሁ ውስጥ ሶስቱ ባለ 66 ኪሎ ቮልት፣ አምስቱ ባለ 132 ኪሎ ቮልት እንዲሁም የተቀሩት ሰባቱ ደግሞ ባለ 230 ኪሎ ቮልት መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

በማከፋፈያ ጣቢያዎቹና በኃይል ማስተላለፊያ መስመሮቹ ላይ የተለያየ መጠን ያላቸው ጉዳቶች በመድረሱ በክልሉ  ለተወሰኑ ጊዜያት  የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋርጦ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

በክልሉ የተለያየ አቅም ያላቸው 1 ሺህ 727 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍኑ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ይገኛሉ ያሉት ኃላፊው  በህግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት በዋናነት በኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች እና በኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ጠቁመዋል፡፡

በሰባት የኃይል ማስተላለፊያ ተሸካሚ ምሰሶዎች ላይ ጉዳት መድረሱን እና በኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ ከፍተኛ የሆነ የመበጣጠስና የኢንሱሌተሮች መሰባበር አደጋዎች እንዳጋጠሙ ገልፀዋል፡፡ የጉዳት መጠኑም በገንዘብ ሲተመን 67 ነጥብ አምስት ሚሊዬን ብር እንደሆነ ነው መግለጫው ያመለከቱት፡፡

በወልቃይት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የሠራተኞች መኖሪያ ቤት፣ ቢሮዎች፣ የዕቃ ግምጃ ቤቶች እና የመለዋወጫ ዕቃዎች ላይ ጉዳት ደርሷል ያሉት አቶ ሞገስ ግምታቸው 15 ሚሊዬን ብር የሚደርስ 5 ተሸከርካሪዎችና የጫኗቸው የመለዋወጫ ዕቃዎች በጁንታው መዘረፋቸውን አንስተዋል፡፡

የተዘረፉት የመለዋወጫ ዕቃዎች በተጀመሩት የጥገና ሥራዎች ላይ አሉታዊ ጫና ከማሳደራቸውም ባሻገር ተቋሙን ለተጨማሪ ወጪ እንደዳረጉትም ነው የተናገሩት፡፡

ለመለዋወጫ እና ሌሎች ተጓዳኝ ዕቃዎች የወጣው ወጪም ከ 11 ሚሊዬን ብር እንደሆነ ነው  ያስታወቁት፡፡

እንደ አቶ ሞገስ ገለፃ በኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ  ላይ የሚገኙና ኢትዮ-ቴሌኮም ከፍተኛ የድምፅ እና የዳታ አገልግሎት የሚሰጥባቸው  የኦ.ፒ.ጂ. ደብሊው ፋይበር መስመሮች ላይ ጉዳት ደርሷል።

በዚህም 178 ኪሎ ሜትር የሚደርስ የኦ.ፒ.ጂ. ደብሊው ፋይበር እንዲሁም 43 የሚሆኑ የኦ.ፒ.ጂ. ደብሊው ፋይበር  ሳጥኖች ላይ ጉዳት መድረሱን ኃላፊው ገልፀዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በኃይል መሠረተ ልማቶቹ ላይ ጉዳት በመድረሱ ምክንያት ተቋሙ ኤሌክትሪክ በማቅረብ ሊያገኝ ይችል የነበረውን 146 ነጥብ 2 ሚሊዬን ብር የሚገመት ገንዘብ ሊያጣ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ከኃይል ሽያጭ ይገኝ የነበረና የባከነ 245 ነጥብ 5 ሚሊዬን ኪሎ ዋት ሰዓት ኢነርጂ  በገንዘብ ሲሰላ ከ140 ሚሊየን ብር በላይ ይሆናል ብለዋል፡፡

አቶ ሞገስ እንዳሉት በክልሉ በተካሔደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ተቋሙ በአጠቃላይ  ከ240 ሚሊዬን ብር በላይ የሚገመት ኪሳራ ገጥሞታል።

በሪጅኑ ካለው 1727 ኪሎ ሜትር የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ውስጥ 2 መቶ ኪሎ ሜትር የሚሆነው ብቻ የፍተሻና ጥገና ስራ እንደሚቀረው  እንዲሁም የሁመራ እና መሰቦ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች የፍተሻና ጥገና ስራ ተጠናቆ ኃይል ለመስጠት ዝግጁ መሆኑ በመግለጫው ተጠቅሷል።

የወልቃይት ማከፋፈያ ጣቢያ ግን መለዋወጫ ዕቃ ስለሚያስፈልገው ከውጭ ለማስገባት በሂደት ላይ ነው።

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

seventeen + fifteen =