በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከኤሌክትሪክ ኤክስፖርት ከ90 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ተገኝቷል

Published by corporate communication on

በተጠናቀቀው የ2013 በጀት ዓመት ለጎረቤት ሀገራት ከተሸጠ የኤሌክትሪክ ኃይል ከ90 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የማርኬቲንግ እና ቢዝነስ ድቨሎፕመንት መምሪያ አስታወቀ፡፡

በበጀት ዓመቱ ለሱዳን እና ጅቡቲ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ኪሎ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ 80 ነጥብ 7 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ኪሎ ዋት ሰዓት በላይ ኤሌክትሪክ በማቅረብ 90 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መሰብሰቡን መምሪያው አስታውቋል፡፡

ይህም ከእቅዱ የ9 ነጥብ 7 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወይም የ12 በመቶ ብልጫ እንዳለው ለማወቅ ተችሏል፡፡

ወደ ሀገራቱ በተናጠል ለሱዳን 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ኪሎ ዋት ሰዓት ኤሌክትሪክ በመሸጥ 55 ነጥብ 48 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ለጅቡቲ ከ5 መቶ 27 ሚሊዮን ኪሎ ዋት ሰዓት ኤሌክትሪክ በመሸጥ 35 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡

ተቋሙ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከውጭ ሃገራት የኃይል ሽያጭ የሰበሰበው ገቢ በ2012 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከሰበሰበው ጋር ሲነፃፀር የ24 ነጥብ 1 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወይም የ36 ነጥብ 2 በመቶ ብልጫ አለው፡፡

በ2013 በጀት ዓመት ለኬንያ 695 ሚሊዮን ኪሎ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ 48 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በኬንያ በኩል እየተገነባ ያለው የኢትዮ ኬንያ የማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት ግንባታ ባለመጠናቀቁ ለኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ አልተቻለም፡፡

ተቋሙ ከውጭ ሃገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ የሚሰበስበው ዓመታዊ ገቢ በየዓመቱ እያደገ የሚገኝ ሲሆን ይህም 2011 በጀት ዓመት ከነበረበት 54 ነጥብ 9 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በ2012 በጀት ዓመት 66 ነጥብ 4 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ያደገ ሲሆን በ2013 በጀት ዓመትም 90 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር መድረስ መቻሉን የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡

የኃይል ማመንጫ ግድቦች በቂ ውሃ መያዛቸው እና የኃይል መቆራረጥ መቀነሱ ለበጀት ዓመቱ እቅድ መሳካት እና በዓመቱ ለተስተዋለው የገቢ አሰባሰብ እድገት በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

seven − five =