በተቋሙ የህብረት ስምምነት እና በማኔጅመንት መተዳደሪያ ደንብ ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እየተካሄደ ነው

Published by Corporate Commnucation on

በተቋሙ የህብረት ስምምነት እና በማኔጅመንት መተዳደሪያ ደንብ ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እየተካሄደ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለተቋሙ አመራሮች፤ በተቋሙ የህብረት ስምምነት እና በማኔጅመንት መተዳደሪያ ደንብ ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

የስልጠናውን መጀመር አስመልክቶ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሰው ኃይል ስራ አስፈፃሚ አቶ አደባባይ ዓባይ አመራሩ የህብረት ስምምነቱን እና የማኔጅመንት መተዳደሪያ ደንቡን በውል ተገንዝቦ በመርህና በተደራጀ መልኩ ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡

ሠራተኛው መብቱን በህግ ሳይጠይቅ ቀድሞ የሠራተኛውን መብት ሊያስጠብቅ የሚችል አመራር መፍጠር ያስፈልጋል ያሉት አቶ አደባባይ ሠራተኛው በበኩሉ የተቋሙን ግብ ለማሳካት ዛሬ ምን ሠራሁ ብሎ ራሱን የሚገመግም ቁመና ሊላበስ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የሰው ኃይል ዳይሬክተር ወይዘሮ ሌንሴ ኤዴኤ በበኩላቸው ውጤታማ የሠው ኃይል መፍጠር የሚቻለው ግዴታውንና መብቱን በደንብ ተገንዝቦ በተደራጀ መልኩ የሚንቀሳቀስ አሰሪና ሠራተኛ ማፍራት ሲቻል ብቻ ነው ብለዋል፡፡

ዳይሬክተሯ የህብረት ስምምነቱን አንኳር ጉዳዮች ባቀረቡበት ወቅት በተዘጉ ወይም ስራ ባቆሙ የስራ ክፍሎች ላይ የሚገኙ የድርጅቱን ሠራተኞች ተቋሙ ወደ ሌላ የሥራ ክፍል አዛውሮ ማሠራት እንደሚችል፤ ሠራተኞች በህመም ወይም በሌላ ምክንያት ከሥራ ገበታቸው ላይ ሳይገኙ ሲቀር ለቅርብ ኃላፊያቸው ማሳወቅ እንደሚገባቸው፤ በአዋጁ መሠረት ቅዳሜ ለሁሉም ሠራተኞች የትርፍ ሰዓት ክፍያ እንደማይከፈል እና የዓመት ፈቃድን በተመለከተ በበጀት ዓመቱ በሁለት የጊዜ መርሀ ግብር ከፍሎ በማስያዝ መጠቀም እንደሚቻል አብራርተዋል፡፡

ወይዘሮ ሌንሴ አክለውም የቅሬታ አቀራረብን በተመለከተ ማንኛውም ሠራተኛ ደርሶብኛል ለሚለው በደል ለቅሬታ መነሻ የሆነውን ውሳኔ ከሰጠው ኃላፊ በደረጃ ቀጥሎ ለሚገኘው የስራ ኃላፊ ማቅረብ ይኖርበታል ያሉ ሲሆን ሠራተኛው ያቀረበው ቅሬታ በ5 ቀናት ውስጥ ምላሽ ካላገኘ ወይም በውሳኔው ካልተስማማ ወደሚቀጥለው ኃላፊ ቅሬታውን ማቅረብ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

የሠራተኞች የዕድገትና የዝውውር ሥራዎች በሚከናወኑበት ወቅት ሠራተኞች የሚለቁበትን እና የሚገቡበትን የስራ ክፍል ኃላፊዎች በማማከር እየሠሩ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የመሠረታዊ ሠራተኛ ማህበር ሰብሳቢ አቶ መኮንን ክፍሌ ናቸው፡፡

ሰብሳቢው እንዳሉት የቅዳሜ ስራ ቀንን በተመለከተ አሰሪና ሠራተኛ አዋጁ አንድ ሠራተኛ በቀን 8 ሰዓት በሳምንት 48 ሰዓት መስራት እንደሚጠበቅበት የሚደነግግ ሲሆን እንደስራው ባህሪ ሊወሰን ይችላል ብለዋል፡፡ 

ከዚህ ጋር በተያያዘ የማኔጅመንት መተዳደሪያ ደንብ ቀርቦ ውይይት የተካሄደ ሲሆን የስራ ኃላፊዎች ሥራቸውን ሲያከናውኑ ህግና መመሪያን መሠረት አድርገው ግልፅ በሆነ መንገድ ሊሆን እንደሚገባ ተመልክቷል፡፡

በተጨማሪም የስራ ኃላፊዎች በሰዓት በሥራ ቦታቸው ላይ በመገኘት ለሠራተኞች አርአያ በሆነ መልኩ እና ሠራተኞችን ለስራ በሚያነሳሳ ሁኔታ ሠርተው ማሠራት እንደሚጠበቅባቸው እንዲሁም ከሙስናና ብልሹ አሰራር ሊፀዱ እንደሚገባ ወይዘሮ ሌንሴ አሳስበዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲሆን በተለያዩ የስራ ኃላፊዎች ምላሽ ተሰጦባቸዋል፡፡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው ግንቦት 15, 2011 ዓ.ም አዲስ አበባ በሚገኘው ግዮን  ሆቴል በመካሄድ ላይ ሲሆን በዛሬው ዕለት ይጠናቀቃል፡፡

Categories: ዜና

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

16 − eleven =

Facebook