በተቋሙ አምስት ዘርፎች ላይ የተቋም ሀብት ዕቅድ ስርዓት – ERP ለመተግበር የሚያግዝ ስልጠና ተጀመረ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ወቅቱ በተመረጡ አምስት ዘርፎች ላይ የተቋም ሀብት ዕቅድ ስርዓት (Enterprise resource planning) ለመተግበር የሚያስችለውን ስልጠና ዛሬ ጀመረ፡፡
የተቋሙ የሞደርናዜሽን ቢሮ ዳይሬክተር አቶ ገነቱ ደሳለኝ እንደተናገሩት ተቋሙ ከኢትዮጰያ አየር መንገድ እና ሳፕ(SAP) ከተባለ ዓለምአቀፍ ኩባንያ ጋር በመተባበር በሶስት ደረጃዎች የተቋም ሀብት ዕቅድ ስርዓት ትግበራ ላይ ሲሰራ ቆይቷል፡፡
በመጀመሪያው ምዕራፍ የተቋሙን ግዙፍ ሃብት የሚያቀሳቅሱት የሰው ኃይል አስተዳደር ፣የማርኬቲንግ እና ቢዝነስ ልማት፣ የፋይናስ፣ የኃይል ማመንጫ ግንባታ እና ኃይል ማከፋፈያ እና ማስተላፊያ ግንባታ ፕሮጀክቶች፣የንብረት አስተዳደር እና የግዢ የስራ ክፍሎችና ዘርፎች መለየታቸውን ተናግረዋል፡፡
በተለዩት ዘርፎችም ያሉባቸውን የአሰራር ክፍተቶችና ችግሮች በመለየት ክፍተቱንና ችግሮቹን የሚሞላ የሶፍትዌር ቴክኖሎጂ በጥናት የማዘጋጅት እንዲሁም የማህደር እና የመረጃ ማሰባሰብ ስራዎች ላለፉት ስምንት ወራቶች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ገልፀዋል፡፡
የተዘጋጀው ስልጠና ለተቋም ሀብት ዕቅድ ስርዓት በተዘጋጁት ሞጁሎች እና ሶፍትዌሮች ላይ የተግባር ልምምድ በመስጠት ዘርፎቹን ወደ ሙሉ ትግበራ በማስገባት ወቅቱ የሚጠይቀውን ዘመናዊ አሰራር ተግባራዊ ለማድረግ እንደሆነ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
የተቋም ሀብት ዕቅድ ስርዓት (Enterprise resource planning) መተግበር ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ ፈጣን ፣ትክክለኛና ቀልጣፋ የመረጃ፣የማህደር፣የፕሮጀክት አስተዳደር፣የፋይናስ፣ የግዢ እና የንብረት አያያዝ እና አስተዳደር እንዲኖር በማድረግ በተቋሙ ያለውን የመረጃና የዶክመንት አያያዝ ችግር ይቀርፋል፡፡
ሪጅኖችና ዘርፎችን ከማዕከል ጋር በመረጃ መረብ በማስተሳሰር እና ብክነትን በማስቀረት ገቢን በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ እንደሚያስችል አቶ ገነቱ አስገንዝበዋል፡፡
ከየስራ ዘርፎቹ የተወጣጡት ሰልጣኞች የተግባር ስልጠና ልምምዱን በአግባቡ በመረዳት እና በመያዝ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡
የተግባር ልምምዱ ሲጠናቀቅ በ2014 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ወደ ትግበራ ለመግባት ዕቅድ ተይዟል፡፡
0 Comments