በባለፉት ዘጠኝ ወራት 8 የተለያዩ ጥቆማዎች ለጽ/ቤቱ ቀርበዋል

ባለፉት ዘጠኝ ወራት 8 የተለያዩ ጥቆማዎችን መቀበሉን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥነ- ምግባርና ጸረ ሙስና መከታተያ ስራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡
የጽ/ቤቱ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መርጋ ተረፈ እንዳስታወቁት ከቀረቡ ጥቆማዎች ውስጥ ሁለቱ የሙስና ወንጀል ባህሪ ያላቸው ሲሆኑ ስድስቱ ደግሞ አስተዳደራዊ እርምጃ የሚሹ ጥቆማዎች ናቸው።
እንደ አቶ መርጋ ገለጻ ሁለቱ የሙስና ወንጀል ጥቆማዎች በተጭበረበረ የኃላፊዎች ፊርማና ማህተም የተፈፀመ የጉዞ አበልና የቀን ሠራተኞች ክፍያ እና ያልተገባ ጥቅም በመፈለግ በሁለት የመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ በመስራት ላይ የነበረ በአንድ የተቋሙ ሠራተኛ ጉዳይ ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡
ጥቆማዎቹ ለፌደራል የሥነ- ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ከሚቀርብ የጥቆማና የመረጃ ስርዓት እንዲሁም በተቋሙ እየተስተዋሉ ያሉ የሙስና ወንጀሎችን የተቋሙ ሠራተኞች እና የውጭ ደንበኞች ጥቆማ እንዲሰጡ በተቀመጠው አሰራር መሰረት የቀረቡ መሆናቸውን አቶ መርጋ አስታውቀዋል፡፡
ለጽ/ቤቱ የሚቀርቡ ጥቆማዎች በአስቸኳይ የሙስና መከላከል ሥራ አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 21/2013 ላይ በተደነገገው መሰረት በመመዘን ትክክለኝነቱን የማጣራት ስራ ሲከናወን እንደነበር ስራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል፡፡
ለጽ/ቤቱ ከቀረቡ ጥቆማዎች ውስጥ ሁለቱ የሙስና ወንጀሎች ለፍትህ አካላት ተልከው የውሳኔ ሀሳብ እየተጠበቀ ሲሆን ሌሎች አስተዳደራዊ እርምጃ የሚሹ ጉዳዮች ደግሞ በተቋሙ ባለሙያዎች ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑን አቶ መርጋ ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተቋሙ ባለሙያዎች ክትትል ሲደረግባቸው ከነበሩ ጉዳዮች መካከል በሁለት ሠራተኞች ላይ የስራ ስንብት፣ በአንድ ሠራተኛና በሁለት የስራ ኃላፊዎች ላይ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እንዲሁም በአንድ ባለሙያና በአንድ የሥራ ኃላፊ ላይ ደግሞ የገንዘብ ቅጣት እርምጃ መወሰዱን ነው ስራ አስፈጻሚው የገለጹት፡፡
በቀረቡ የሙስና ወንጀል ጥቆማዎች ላይ ክትትል ከማድረግ በተጨማሪ ለአስተዳደራዊ ችግሮች በሚያጋልጡ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ የአሰራር ስርዓት ማስተካከያዎች መደረጋቸውንም አቶ መርጋ ጠቁመዋል፡፡
እንደ አቶ መርጋ ገለጻ በዕቃ ግምጃ ቤት የንብረት አያያዝ እና ጥበቃ፤ በንብረት አወጋገድ የጨረታ ሂደት፣ በፕሮጀክትና ኦፕሬሽን መካከል የሚደረግ የንብረት ርክክብ፤ በፋይናንስ የክፍያ አፈፃፀም እና በውክልና አሰጣጥ ላይ፤ በትምህርትና ስልጠና የመረጣ ሂደት፤ በዓመት ፍቃድ አሰጣጥ እና በሰዓት መቆጣጠሪያ አያያዝ ፣ በማከፋፈያ ጣቢያ የጥበቃ ኃላፊዎች ምደባ የአሰራር ስርዓት ላይ ማስተካከያ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡
የሙስና ትግሉን በጥናትና በመረጃ ላይ በመመስረት እንዲከናወን ለማድረግ በሥራ ዘርፉ ውስጥ የአሰራር ጥናትና አስቸኳይ የሙስና መከላከል እና የስልጠና፣ ኮሙዩኒኬሽንና ሀብት ምዝገባ የሚሉ ሁለት የሥራ ክፍሎችን የማደራጀት ስራ መሰራቱንም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
በሥነ-ምግባር ግንባታ፣ በሙስና ተጋላጭነት ጥናትና መረጃ አገልግሎት ላይ የበለጠ በመስራት በቀጣይ ተቋሙን ከሙስናና ብልሹ አሰራር የፀዳ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራም አቶ መርጋ አረጋግጠዋል፡፡
የሙስና ወንጀል ውስብስብና ረቂቅ በመሆኑ ድርጊቱን በሥራ ክፍሉ ባለሙያዎች ብቻ መግታት ስለማይቻል በባለሙያዎች በሚደረገው የሥነ-ምግባር ግንባታ፣ የሙስና ተጋላጭነት ስጋት ጥናትና የሙስና መረጃ አገልግሎት ሥራ ላይ የተቋሙ ሠራተኞችና የስራ መሪዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ አቶ መርጋ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
0 Comments