በበጀት ዓመቱ 28 የቴክኒክ እና የፋይናንስ ኦዲቶችን ለማከናወን እቅድ ተይዟል

Published by corporate communication on

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በተያዘው የበጀት ዓመት 28 ቴክኒካልና የፋይናንስ ኦዲት ምርመራ ለማከናወን አቅዶ እየተሰራ መሆኑን የተቋሙ የውስጥ ኦዲት መምሪያ አስታወቀ፡፡

የመምሪያው ዳይሬክተር አቶ ገ/እግዚአብሔር መዝገበ እንዳስታወቁት የኦዲት ምርመራው በተቋሙ ስር የሚገኙ ሁሉንም የስራ ዘርፎችና መምሪያዎችን ባካተተ መልኩ ይካሄዳል፡፡

የኦዲት ምርመራው በተቋሙ ያለውን የስጋት አስተዳደር፣ የመልካም አስተዳደርና የቁጥጥር ስርዓቱ በመፈተሽ ለሚስተዋሉ ክፍተቶች የማሻሻያ ሀሳብ ለማቅረብ እንዲሁም ተቋሙ በበጀት ዓመቱ ለማከናወን ያቀዳቸውን ተግባራት ከግብ ለማድረስ እንደሚያግዝ ተመላክቷል፡፡

በበጀት ዓመቱ የሂሳብና የቴክኒክ ኦዲት ምርመራ ለማካሔድ የስጋት አባቢዎችን በመለየት፣ ለተቋሙ ያላቸው ፋይዳ እንዲሁም ከዚህ ቀደም የኦዲት ምርመራ ያልተደረገባቸውን ጉዳዮች መነሻ በማድረግ  ምርመራ ለማከናወን መታቀዱን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

የምርመራ ስራዉ የሚሸፍነው ጊዜ እንደ ኦዲት የምርመራ ዓይነቱ የሚለያይ መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ ከዚህ ቀደም ኦዲት የተደረገ የስራ ዘርፍ የኦዲት ምርመራው የሸፈነው ጊዜ ያበቃበትን መነሻ በማድረግ የኦዲት ሥራው ይከናወናል ብለዋል፡፡

ከዚህ በፊት ኦዲት ያልተደረጉ ፕሮጀክቶችም ፕሮጀክቶቹ ከተጀመሩበት ጊዜ አንስቶ እንዲሁም በኦፕሬሽንና ሌሎች ዘርፎች ላይ የሚከናወነው የኦዲት ምርመራ ስራ የኦዲት ምርመራው እስከሚሰራበት ጊዜ ድረስ ያለውን እንደሚሸፍን ኃላፊው ገልፀዋል፡፡

ከፋይናንስና የቴክኒክ የኦዲት ምርመራ ስራዎች በተጓዳኝ በበጀት ዓመቱ የአመራሩንና እና የሠራተኞችን ተግባራትና አፈፃፀም ከተቋሙ ፖሊሲ፣ ደረጃ፣ የአፈፃፀም ስርዓት እና ተፈፃሚነት ሊኖራቸው ከሚገቡ ህጎች፣ ፕሮግራሞች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ጋር የተጣጣመ መሆኑን መመርመርና በሚታዩ ክፍተቶች ላይ የማሻሻያ ሃሳቦችን ለማቅረብ እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ በበጀት ዓመቱ በተቋሙ የሚፈጸሙ ግዥዎች የድርጅቱን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ መከናወናቸው ይጠናል፡፡

የተቋሙን የጥናት፤ ዲዛይን፣ የፕሮጀክቶች ግንባታ ክትትልና የቁጥጥር ስራዎችን፣ የኃይል ብክነትን ቅነሳ ፍተሻ፣ የመደበኛና የአስቸኳይ ጥገና ስራዎች በተገቢ ሁኔታ መከናወናቸው፤ የገቢ አሰባሰብ እና የወጪ/የክፍያ አስተዳደር ስርዓቱን የማየት እና ወጪን ለመቀነስ በተቋሙ መከናወን ያለባቸው ስራዎች መከናወናቸውንና እና ያስገኙት ዉጤቶችን የመመርመር ስራዎች በበጀት ዓመቱ ትኩረት የሚደረግባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በተጠናቀቀው የ2013 በጀት ዓመት በተመረጡ የስራ ክፍሎች እና ፕሮጀክቶች ላይ 35 የኦዲት ምርመራ ሥራዎች መከናወናቸውንና በተለያዩ ጊዚያት ከተደረጉ የኦዲት ሪፖርቶች መካከል የ66ቱ ሪፖርቶች የግኝት መከታተያ መዘጋጀቱን ዳይሬክተሩ አንስተዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት ለማከናወን የታቀደውን የኦዲት ስራ በጥራት ለማከናወን የስራ ክፍሉን በሰለጠነና ብቃት ባለው የሰው ኃይል ለማደራጀት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ሁሉም አመራርና ሠራተኛ የኦዲት ምርመራው የሚከናወነው ለተቋሙ ግብ ስኬት መሆኑን ተገንዝቦ ለስራው አስፈላጊ እገዛ እንዲያደርጉ ዳይሬክተሩ ጠይቀዋል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

one + four =