በቀጣዮቹ 10 ዓመታት የማመንጨት አቅምን ከ17 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ ለማድረስ እየተሰራ ነው
በቀጣዮቹ 10 ዓመታት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅምን ከ17 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ ለማድረስ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የዋና ሥራ አስፈፃሚ የቴክኒክ አማካሪ አስታወቁ፡፡
አማካሪው ኢንጂነር አንዳርጌ እሸቴ እንደገለፁት በአሁኑ ሰዓት በሀገሪቱ ያለዉ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም 4 ሺህ 528 ሜጋ ዋት ደርሷል፡፡
በቀጣዮቹ 5 ዓመታት 13 ሺህ ሜጋ ዋት እንዲሁም በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ከ17 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ ለማድረስ ዕቅድ ተነድፎ እየተራ ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከጀመረ ከአንድ ምዕተ ዓመት የዘለለ ዕድሜ ቢያስቆጥርም የኤሌክትሪክ ኃይል ሽፋኑ ግን ከ44 በመቶ እንዳልዘለለ ኢንጂነር አንዳርጌ ገልፀዋል፡፡
የዚህም ምክንያቱ በተለያዩ ምክንያቶች በሃገሪቱ ያለው የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ያለመስፋፋቱ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
እንደ አማካሪው ገለፃ ከዚህ በፊት የነበረው የኢነርጂ ፖሊሲ የግል ባለሃብቶች በኃይል ልማት ዘርፉ ላይ እንዲሳተፉ የሚጋብዝ ባለመሆኑ ለኃይል ማመንጨትና እቅም ማነስና ለተደራሽነት ሽፋኑ ማነስ ምክንያት ሆኖ ቆይቷል፡፡
በመንግስት አቅም ብቻ እቅዱን ማሳካት እንደማይቻል የተናገሩት ኢንጂነር አንዳርጌ ከዚህ ጎን ለጎንም በግልና የመንግስት አጋርነትን መርሃግብር የግል አልሚዎች በኃይል ልማት ዘርፍ እንዲሰማሩ ይደረጋል ብለዋል፡፡
በዚህም በዕቅዱ የተያዘውን የማመንጨት አቅም ለማሳካት ተስፋ ተጥሎበታል ሲሉ ገልፀዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለኤሌክትሪክ ኃይል የሚውል በርካታ የታዳሽ ኃይል ምንጭ ያላት ሲሆን በአሁኑ ወቅትም የግል ባለሃብቱ በአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ፣ በዲቼቶና ጋድ የፀሃይ ኃይል እና በኮርቤቴ የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ላይ ተሳታፊ መሆን ጀምረዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በመላው ሀገሪቱ የዲዝል መጠባበቂያ ኃይል ማመንጫዎችን ጨምሮ 23 ማመንጫ ጣቢያዎችን ያስተዳድራል፡፡
ኢንጂነር አንዳርጌ እንደገለፁት መሰረተ ልማቶችን ለማስፋፋት በሚከናወነው ሥራ ለፕሮጀክቶች ግንባታ የሚመረጡ ቦታዎችን ከወሰን ማስከበር በወቅቱ ነፃ በማድረግ፣ መመሪያ ከሚፈቅደው በላይ ተገቢ ያልሆነ የካሳ ጥያቄ ባለማቅረብና በመሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀሙ የስርቆት ወንጀሎችን በመከላከል ህብረተሰቡ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል፡፡
0 Comments