በቀጣዮቹ አስር ዓመታት የሚተገበር የሲስተም ልማት ዕቅድ ተዘጋጅቷል

Published by corporate communication on

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በቀጣዮቹ አስር ዓመታት ለመተግበር ባዘጋጀው የሲስተም ልማት ዕቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመምከር ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡

በዕቅዱ መሰረት ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅሙን ከ4 ሺህ 515 ሜጋዋት ወደ 17 ሺህ 56 ሜጋዋት ለማሳደግ፣ የከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ መስመሮችን ርዝመት አሁን ካለበት19 ሺህ 746 ኪ.ሜ. ወደ 33 ሺህ 497 ኪ.ሜ. ለማድረስ ታቅዷል፡፡

በተቋሙ የኮርፖሬት ፕላኒንግ ዘርፍ የተዘጋጀው የአስር ዓመት ዕቅድ እንደሚያሳየው በዕቅድ ዘመኑ ከ132 ኪሎ ቮልት በላይ አቅም ያላቸው 176 ማከፋፈያ ጣቢያዎችን ቁጥር ወደ 265 ለማሳደግም ይሰራል፡፡

በኃይል ማስተላለፍ ወቅት የሚያጋጥመውን የ6 በመቶ የኤሌክትሪክ ብክነት ወደ 3 ነጥብ 5 በመቶ ለመቀነስና የተቋሙን ገቢ ደግሞ ከ300 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወደ 5 ነጥብ 32 ቢሊየን ለማሳደግ ዕቅድ ተይዟል፡፡

አሁን ከግሪድ ጋር ያለውን የ33 በመቶ ግንኙነት ወደ 96 በመቶ ለማሳደግ፤ ከውሃ የሚገኘውን የ93 በመቶ የማመንጨት ድርሻ ወደ 73 በመቶ በመቀነስ በአንፃሩ ከንፋስ፣ ከጂኦተርማልና ከፀሐይ ኃይል የማመንጨት ድርሻን ለማሳደግ እንደሚሰራም በዕቅዱ ተመላክቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት 24 ማከፋፈያ ጣቢያዎች እና  3 ሺህ 740 ኪ.ሜ. ርዝመት ያለው የማስተላለፊያ መስመር በግንባታ ላይ ሲሆን የ79 ማከፋፈያ ጣቢያዎችና 4 ሺህ 130 ኪ.ሜ ርዝመት ያለው ማስተላለፊያ መስመር የአዋጭነት ጥናት ተጠናቋል፡፡

የ 60 ማከፋፈያ ጣቢያዎችና 5 ሺህ 880 ኪ.ሜ. ርዝመት ያለው ማስተላለፊያ መስመር የአዋጭነት ጥናት ለማከናወን በዕቅድ ተይዟል፡፡

ግንባታቸው የተጀመሩትም ሆነ የአዋጭነት ጥናታቸው የተጠናቀቁት ፕሮጀክቶች የኤሌክትሪክ መሠረተልማቶችን በመላው ሀገሪቱ በፍትሐዊነት ለማዳረስ የሚያስችሉ ናቸው፡፡

የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት 35 ነጥብ 9 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ወይም 1 ነጥብ 36 ትሪሊየን ብር ያስፈልጋል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

5 × two =