በቀጣይ 10 ዓመታት ለኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች 40 ቢሊየን ዶላር ያስፈልጋል

በቀጣይ 10 ዓመታት ከተለያዩ የኃይል አማራጮች 71 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ፕላኒንግ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አንዱአለም ሲዓ ገለፁ፡፡
ፕሮጀክቶች ለመገንባት 40 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስፈልግም ሥራ አስፈፃሚው ገልፀዋል፡፡
እንደ አቶ አንዱአለም ገለፃ ለፕሮጀክቶቹ ያስፈልጋል ተብሎ የታሰበው ገንዘብ በግልና በመንግስት አጋርነት፣ በአፍሪካ ልማት ባንክ፣ በአለም ባንክ፣ በሌሎች የልማት አጋሮችና አበዳሪ ተቋማት፣ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እንዲሁም በኢትዮጵያ መንግስት ይሸፈናል ተብሎ ዕቅድ ተይዟል፡፡
በ10 ዓመቱ ውስጥ ይገነባሉ ተብለው በዕቅድ ከተያዙ ፕሮጀክቶች መካከልም 16 የውሃ፣ 24 የነፋስ፣ 17 የእንፋሎት እንዲሁም 14 የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች መሆናቸውን ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡
አቶ አንዱአለም እንዳሉት በዕቅድ የተያዙትን የኃይል ፕሮጀክቶች ግንባታ በመንግስት ብቻ ማሳካት ስለማይቻል በአሁኑ ሰዓት የግልና የመንግስት አጋርነት ስትራቴጂ ተቀርፆ በመሰራት ላይ ይገኛል፡፡
ይገነባሉ ተብለው ከተለዩት ፕሮጀክቶች መካከል የትኞቹ ፕሮጀክቶች ቀድመው መገንባት እንዳለባቸው እና የትኞቹ በአነስተኛ ዋጋ መገንባት እንሚችሉ የመለየት ስራ እንደሚከናወንም አቶ አንዱአለም አብራርተዋል፡፡
ማመንጫ ፕሮጀክቶች በግል አልሚዎች እና በግልና በመንግስት ሽርክና እንዲገነቡ በተያዘው አቅጣጫ መሰረት ሁለት የፀሐይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች አኳ ፓወር በተሰኘ የሳዑዲ አረቢያ ኩባንያ የሚገነቡ ሲሆን ኩባንያው ወደ ግንባታ ለመግባት በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
የአይሻ 1 የነፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን ግንባታ ለማከናወንም አሚያ ከተሰኘ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ኩባንያ ጋር ድርድር መጀመሩን የጠቆሙት አቶ አንዱአለም የሌሎች የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች አልሚን ለመለየት በጨረታ ሂደት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
እንደ አቶ አንዱአለም ገለፃ የቱሉሞየና ኮርቤቲ የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በግል አልሚዎች አማካኝነት ግንባታቸው ተጀምሯል፡፡
0 Comments