በሳይት ላይ መስራት ያለበት ሥራ ተሰርቷል – የፕሮጀክቱ የሳይት ሥራ አስኪያጅ

Published by corporate communication on

የአይሻ II የንፋስ ኃይል ፕሮጀክት ከሚኖሩት 48 የንፋስ ተርባይኖች መካከል የአርባዎቹን ተርባይኖች ተከላና የፍተሻ ሥራ በተያዘው በጀት ዓመት በማጠናቀቅ ከብሔራዊ የኃይል ቋት ጋር ለማገናኝት እየሰራ መሆኑን የፕሮጀክቱ የሳይት ሥራ አስኪያጅ ገለፁ፡፡

ሥራ አስኪያጁ አቶ ሙሉቀን ተሰማ እንደገለፁት በፕሮጀክቱ 120 ሜጋ ዋት ለማመንጨት ከሚተከሉት 48 የንፋስ ተርባይኖች መካከል የ24ቱ ተከላ ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል፡፡

ሁሉንም ተርባይኖች ለመትከል የሚያስችል የመሠረት ቁፋሮና የኮንክሪት ሙሌት ስራ መጠናቀቁን ገልፀዋል፡፡

አራት ተርባይኖችን ለመትከልም ንፋስ የሚቀንስበት ወቅት እየተጠበቀ መሆኑንና ተጨማሪ አራት ተርባይኖች ደግሞ ከወደብ ወደ ፕሮጀክት ሳይቱ እየተጓጓዙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አቶ ሙሉቀን እንደገለፁት በሳይት ላይ መስራት ያለበት ሥራ የተሰራ በመሆኑ ቀሪዎቹን 16 ተርባይኖች በማምረት ተከላውን ለማከናውን አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል፡፡

ከተወሰኑ የማጠናቀቂያ ሥራዎች በቀር የፕሮጀክቱ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታም ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱን በ 50 ወራት ጊዜ ውስጥ እስከ መጋቢት 2013 ዓ.ም. ለማጠናቀቅ ዕቅድ ቢያዝም በኮቪድ 19 ምክንያት ለፕሮጀክቱ የሚሆኑ ዕቃዎች ፍብረካና ማጓጓዝ እንዲሁም ባለሙያዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት ባለመቻሉ፣ አበዳሪው የቻይና ኤግዚም ባንክ ገንዘብ በጊዜ ባለመልቀቁና በተደረገው የዲዛይን ማሻሻያ ምክንያት ፕሮጀክቱ ምናልባት ከ6 ወር ላላነሰ ጊዜ ሊዘገይ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

የፕሮጀክቱ የሲቪል ሥራ 94 በመቶ፣ የተርባይን ጀነሬተሮች ፍብረካ እና ማጓጓዝ 70 በመቶ፣ የፍተሻና ሙከራ ሥራ 47 በመቶ፣ አጠቃላይ የፕሮጀክቱ አፈፃፀም ደግሞ 70 ነጥብ 25 በመቶ ደርሷል፡፡

የአይሻ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በሶማሌ ክልል አይሻ ወረዳ ከ257 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

14 − 3 =