በራስ አቅም ጥገና የቆሙ ዩኒቶችን ወደ ሥራ ማስገባት መቻሉ ተገለፀ

በጊቤ 2 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ካሉት አራት ዩኒቶች መካከል በዩኒት አንድ እና በዩኒት ሦስት ላይ ሙሉ ጥገና በመደረጉ ተጨማሪ 180 ሜጋ ዋት ማግኘት መቻሉን የጣቢያው ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ገረመው ገልፀዋል።
ጣቢያው በ2002 ዓ.ም ተመርቆ በይፋ ስራ የጀመረ ሲሆን እያንዳንዳቸው 105 ሜ.ዋ የማመንጨት አቅም ያላቸው አራት ዩኒቶች ያሉትና በድምሩ 420 ሜ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው ነው፡፡
በዩኒት አንድና ሦስት ላይ ኃይል እንደመጫን አቅማቸው ውሃን ለመመጠን በሚያገለግለው የፓወር ኖዝል መቆጣጠሪያ (needle valve) ብልሽትና እና ወደ ተርባይን የሚገባውን ውሃ በሚቆጣጠሩ የዘይት ፍሰት መቆጣጠሪያ ሲሊንደሮች (MIV servomotor piston cylinder) ላይ የዘይት መፍሰስ ችግር በማጋጠሙ ዩኒት አንድ ሙሉ ለሙሉ ሲያቆም ዩኒት ሦስት ደግሞ 1/4ኛውን ብቻ ኃይል ያመነጭ እንደነበር የጣቢያው ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አውስተዋል፡፡
ዩኒቶቹ በሙሉ አቅማቸው እንዳያመነጩ ያደረጓቸውን ችግሮች መለየት ከተቻለ በኋላ በቅድሚያ ከተቋሙ የተለያዩ ክፍሎች በተለይም ከክላስተር ቢሮዎች፣ ከቴክኒክ ድጋፍ ክፍል እና ከኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የጥገና ቡድን በማዋቀር ወደ ስራ መገባቱን ኃላፊው ገልፀዋል፡፡
የጥገና ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ወደ ስራ በመገባቱ ዜሮ የነበረውን የዩኒት አንድ የመጫን አቅም ወደ 105 ሜ.ዋ እንዲሁም 25 ሜ.ዋ ብቻ ይጭን የነበረውን ዩኒት ሦስት ወደ 100 ሜ.ዋ ኃይል እንዲያመነጭ በመደረጉ ጣቢያው 180 ተጨማሪ ኃይል እንዲያገኝ አስችሎታል ብለዋል።
በቀጣይም በዪኒት ሁለትና አራት ላይ የፍተሻና የጥገና ስራው የሚሰራ መሆኑን ጠቁመው ጣቢያው የሚጠበቅበትን ኃይል ማምረት እንዲችል በምስራቅ አፍሪካ የጀርመን ተራድኦ ድርጅት (Voith) አማካኝነት በኢትዮጵያውያን ሠራተኞች የጥገና ማኔጀመንት ስርዓት (maintenance management system) ስራዎች እየተሰራ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል።
የጥገና ሥራው በራስ አቅም መከናወኑ ተቋሙ ለውጭ ሙያተኞችና ኩባንያዎች በሚሊየን ሊያወጣ የሚችለውን ውጭ ማስቅት ከማስቻሉ በተጨማሪ ቅንጅታዊ አሰራር እና የእውቀት ሽግግር የተገኘበት እንደነበር ገልፀው ለጥገና ሥራው ለሚጠየቁ የዕቃ እና ተያያዥ አቅርቦቶች የተቋሙ ማኔጅመንት ለሰጠው ፈጣን ምላሽና አዎንታዊ ድጋፍ ምስጋናቸውን በማቅረብ ድጋፉ በቀጣይም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡
0 Comments