በሪጅኑ ያሉት ማከፋፈያ ጣቢያዎች በጥሩ ሁኔታ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የምዕራብ ሪጅን በአካባቢው የሚፈጠሩ የኢንቨስትመንት ዘርፎችን ለማስተናገድ የሚያግዝ በቂ የኤሌክትሪክ አቅርቦት መኖሩን አስታወቀ።
የሪጅኑ የትራንስሚሽንና ሰብስቴሽን ኦፕሬሽንና ጥገና ዳይሬክተር አቶ ቶማስ መለሰ እንደተናገሩት በሪጅኑ ውስጥ የሚገኙ ማከፋፈያ ጣቢያዎች አሁን ያለውንና ሊመጣ የሚችለውን የኃይል ፍላጎት ለማስተናገድ አቅም አላቸው፡፡
በመሆኑም በሪጅኑ ውስጥ የሚገኙትን የተለያየ የኪሎ ቮልት አቅም ያላቸው 11 ማከፋፈያ ጣቢያዎችን አቅም ማሳደግ ሳያስፈልግ በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ የሚቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
በሥራ ላይ ያሉት ማከፋፈያ ጣቢያዎች በአሁኑ ወቅት በጥሩ ሁኔታ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
በአሁኑ ሰዓት በሪጅኑ ለህብረተሰቡ እየቀረበ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል በአማካይ 1 መቶ 16 ሜጋ ዋት መሆኑን የገለፁት ዳይሬክተሩ በቀጣይ ኢንቨስተሮች ወደ አካባቢው ቢገቡም ጥያቄያቸውን ማስተናገድ የሚያስችል የኤሌክትሪክ አቅርቦት መኖሩን ጠቁመዋል።
ይሁንና በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል በመኖሩ ብቻ የኃይል ፈላጊውን ጥያቄ መመለስ ስለማይቻልና በመስመር ብልሽት ምክንያት የኃይል መቆራረጥ እንዳይከሰት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በቅርበት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ሪጅኑ ከማከፋፈያ ጣቢያዎች በተጨማሪ የተለያየ የኪሎ ቮልት መጠን ያላቸውን ከ2 ሺህ 58 ኪሎ ሜትር በላይ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን በማስተዳደር የፍተሻ እና አስቸኳይ የጥገና ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ነው ዳይሬክተሩ የገለፁት።
እንደ አቶ ቶማስ ገለፃ ሪጅኑ ለምዕራብ ፣ ምስራቅ፣ ሆሮጉድሩ እና ቄለም ወለጋ ዞኖች እና ለቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል እንዲሁም ለምዕራብ ሸዋ ዞን የተወሰኑ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ላይ ይገኛል።
0 Comments