በማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የቆጣሪ ገጠማ ሥራ በመከናወን ላይ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የቆጣሪ ገጠማ ስራ በማከናወን ላይ መሆኑን በተቋሙ የስማርት ሜትር ፕሮጀክት ቢሮ ስራ አስኪያጅ አስታወቁ፡፡
ሥራ አስኪያጇ ወ/ሮ ሃይማኖት ተፈራ እንደገለጹት ተቋሙ 130 በሚሆኑ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የቆጣሪ ገጠማ ስራ በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
የቆጣሪዎቹ መገጠም የተቋሙ ደንበኞች ለተጠቀሙት ኃይል ትክክለኛውን ክፍያ እንዲከፍሉ ለማድረግ እንደሚያግዝ ስራ አስኪያጇ አስታውቀዋል፡፡
ይህም ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከዚህ ቀደም በ40/60 የክፍፍል ስምምነት መሰረት የሚገኘውን ክፍያ በማስቀረት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የወጣውን ኃይል ቆጥሮ በማስከፈል የተቋሙን ገቢ ለማሳደግ ይጠቅማል ብለዋል፡፡
እንደ ወ/ሮ ሐይማኖት ገለፃ የቆጣሪ ገጠማ ስራው የኃይል ብክነትን ለመለየት እና አስፈላጊውን የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድም ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡
በመገጠም ላይ የሚገኙት ቆጣሪዎች በእንግሊዝ ሀገር የተመረቱ “CEWE Prometer 100” የተባሉ ሲሆን የገጠማ ስራውንም “Siemens Proprietary Limited” የተባለ ድርጅት በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
ድርጅቱ 1 ሺ 476 ቆጣሪዎችን እንዲያቀርብ ስምምነት ላይ መደረሱን የጠቀሱት ወ/ሮ ሐይማኖት ከዚህ ውስጥ 1 ሺ 226 ቆጣሪዎች በጣቢዎች ላይ የሚገጠሙ ሲሆን ቀሪ 250 ቆጣሪዎች ደግሞ ለመጠባበቂያነት የሚያገለግሉ ናቸው ብለዋል፡፡
በጣቢያዎች ላይ ለመግጠም ከታሰቡ ቆጣሪዎች መካከል ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ድረስ በ42 ጣቢያዎች ላይ 353 ቆጣሪዎች ተገጥመው የሙከራና የፍተሻ ስራ በመከናወን ላይ ነው፡፡
እንደ ስራ አስኪያጇ ገለፃ በእያንዳንዱ ማከፋፈያ ጣቢያ የሚገጠመው የቆጣሪ ብዛት እንደ ጣቢያው ወጪ መስመር ብዛት የሚወሰን ይሆናል፡፡
የቆጣሪዎች ተከላ የዲዛይን፣ የማምረት እና የማጓጓዝ ስራው በ2012 በጀት ዓመት የተገባደደ መሆኑን ያነሱት ወ/ሮ ሐይማኖት እስከ ታህሳስ 2013 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ የገጠማ ስራውን ለማጠናቀቅ እቅድ መያዙን ተናግረዋል፡፡
በቆጣሪ ገጠማ ስራው ላይ ከተቋሙ የተለያዩ የሥራ ክፍሎች የተውጣጡ ባለሞያዎች እንዲሳተፉ መደረጉን የተናገሩት ስራ አስኪያጇ ይህም በቀጣይ ለሚከናወኑ የቆጣሪ ገጠማ ስራዎች በራስ አቅም ለመስራት የሚያስችል ልምድ ለማግኘት ታስቦ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ በ130 ጣቢያዎች ላይ ለሚከናወነው የቆጣሪ ገጠማ አጠቃላይ ስራ የአቅርቦት፣ የተከላ፣ የፍተሻና ሙከራ ስራዎች ለማከናወን በዓለም ባንክ የሚሸፈን ከ25 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ብር እና ከ2 ነጥብ 17 ሚሊዮን በላይ የአሜሪካ ዶላር በጀት ተይዞለታል፡፡
0 Comments