በሚቀጥሉት 5 ዓመታት ኢትዮጵያ ከ10 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ይኖራታል

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ በሚቀጥሉት 5 ዓመታት ኢትዮጵያ ከ10 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም እንደሚኖራት የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚንስትሩ ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ አስታወቁ፡፡
ሚኒስትሩ ዛሬ በዌቢናር በተካሄደው የዩይትድ ኪንግደምና የአፍሪካ የኢነርጂ ሚኒስትሮች ሲምፖዚየም ላይ እንደገለፁት በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ደግሞ ኢትዮጵያ 20 ሺህ ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የሚያስችል አቅም ለመፍጠር አቅዳ እየሰራች ነው።
ኢትዮጵያ እስካሁን 6ዐ በመቶ የሚሆኑት ዜጎቿ የኃይል ተጠቃሚ እንዳልሆኑና የኃይል አቅርት ችግሩ ሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን እያስከተለ እንደሆነም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
ይሁንና ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለመቀየር መንግስት የተለያዩ እቅዶችን በማውጣት እየሰራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ2025 ኢትዮጵያ በግሪድና በኦፍ ግሪድ ለዜጎች ሙሉ በሙሉ ኃይል ለማቅረብ ማቀዷን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
ዘርፉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪና ቴክኖሎጂ የሚጠይቅ በመሆኑ እንደ ዩናይትድ ኪንግደም ያሉ ሃገራት ባለሃብቶች በዘርፉ ገብተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሲምፖዚየሙ ላይ የኢትዮጵያ፣ የሞሮኮ፣ የግብጽ፣ የሞዛምቢክና የሞሪታኒያ ሃገራት የኢነርጂ ሚንስትሮች ንግግር ያደረጉ ሲሆን 183 ባለድርሻዎችም የዌቢናር ውይይቱን ታድመውታል፡፡
0 Comments