የዋና ሥራ አስፈጻሚ መልዕክት

ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ፈጣንና ተከታታይ ሁለንተናዊ ዕድገት ማስመዝገብ ችላለች፡፡

ለእነዚህ የልማት ትሩፋቶች የኤሌክትሪክ ኃይል የማይተካ ሚና ተጫውቷል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እንደ አዲስ ከተቋቋመ ስድስት ዓመታት ያስቆጠረ መ/ቤት ሲሆን፤ በእነዚህ ዓመታት ውስጥም በርካታ ስራዎችን ማከናወን ችሏል፡፡

በተለይም ተቋሙ እንዲያከናውን በአዋጅ ከተሰጡት አበይት ተልዕኮዎች መካከል የኃይል ማመንጫዎች ግንባታ ዋነኛ ተግባሩ ሲሆን በዚህ ረገድም ከውሃ፣ ከንፋስ፣ ከደረቅ ቆሻሻ እና ከጂኦተርማል የኃይል አማራጮች የተለያዩ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡

ከእነዚህ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች መካከልም በ2009 ዓ.ም. በይፋ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የጊቤ III የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫን ጨምሮ፡-

  • የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሥራ 84 በመቶ
  • የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት 44.7 በመቶ የተከናወኑ ሲሆን
  • ባለ 500 ኪ.ቮ የኢትዮ-ኬንያ እና ባለ 400 ኪ.ቮ የገናሌ ዳዋ III ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ግንባታ በመገባድድ ላይ ናቸው፡፡

እንደዚሁም የሚመነጨውን የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ ብሔራዊ የኃይል ቋት እንዲገባ በማገዝ ረገድ ጉልህ ድርሻ ያላቸውን በርካታ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች እና የኃይል ማከፋፈያ ፕሮጀክቶች በመገንባት ላይ ይገኛሉ፡፡

የሃገሪቱን የኃይል ፍላጎት ከማሟላት ጎን ለጎን ከፍጆታ የሚተርፈውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለውጭ ገበያ በማቅረብ የማይናቅ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት ከማስቻሉም በላይ አህጉራዊ የምጣኔ ሃብት ትስስር የተሻለ እንዲሆን የሚያደርገውን አስተዋፅ ኦያሳድገዋል፡፡

እነዚህንና ሌሎች በርካታተ ግባራትን በማከናወን ድርጅታችን የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ለማሳደግ የያዘውን ግብ ከፍተኛ በሚባል ደረጃ ማሳካት ችሏል፡፡ በመሆኑም ተቋማችን የተጀመሩና ያልተጠናቀቁትን ተግባራት በተሻለ መንገድ እንዲፈፀሙ በማድረግ በአሁኑ ጊዜ ያለውን 4260 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

በተለይም በኃይል ልማቱ ዘርፍ የሀገር ውስጥም ሆኑ የውጭ ባለሀብቶች ከመንግስት እና ከግሉ ባለሃብት ጋር በሽርክና በጋራ መስራት የሚችሉበትን (Public private partnership) መደላድል፣ ፖሊሲ እና የህግ ማዕቀፎች ተዘጋጅተው በሚኒስትሮች ምክር ቤት እና ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቀው ሥራ ላይ እንዲውሉ ተደርጓል፡፡

በመሆኑም ይህ የአሰራር ስርዓት ተግባራዊ እንዲሆን መደረጉ ለኃይል ልማት ስራዎች ተጨማሪ አቅም ከመፍጠሩም በላይ የሀገር እና የውጭ ሀገር አልሚዎች በጋራ የዳበረና የበለፀገ ዕውቀት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ የሚያስችል ይሆናል ተብሎ በሰፊው ይታመናል፡፡

በዚህም መሰረት በመንግስትና የግል አጋርነት (መግአ) ቦርድ አስራ ሶስት የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች የተመረጡ ሲሆን ከአስራሶስቱ ስድስት የሶላር ፕሮጀክቶች ወደ ጨረታ እንዲገቡ ውሳኔ አግኝተዋል፡፡ ቀሪዎችም በተመሳሳይ መልኩ ለመግአ ቦርድ እየቀረቡ የሚፀድቁ ይሆናል፡፡

በቀጣይም ለንፋስ ኃይል ፕሮጀክቶች ልማት የሚያስፈልጉ ጥናቶች በማካሄድ በቂ የንፋስ ኃይል የሚገኝባቸውን ስራዎች የመለየት፣ የቅኝት እና ቅድመ ጥናቶች (Reconnaissance and feasibility studies) እንዲሁም የጨረታ ሰነዶች ዝግጅት ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው፡፡

ስለሆነም ይህንን ሰፊ ዕቅድ ከግብ ለማድረስ ሁሉም የተቋሙ አመራሮችና ሠራተኞች ተቋሙ የሚፈልገውን የኮርፖሬት ቢዝነስ አስተሳሰብበ መላበስና ዘመናዊ አሰራር በመዘርጋት፣ በቀጣይነት የሚማርና የሚያድግ ተቋም ለመገንባት እጅ ለእጅ ተያይዘን ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ የሚጠበቅብን መሆኑን ለማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡