ስለ ኢኤኃ ባጭሩ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አመሰራረት

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ መብራት ኃይል ባለሥልጣን (በቀድሞ የእንግሊዝኛ ምዕፃሩ EELPA) በ1948 ዓ.ም. የተመሰረተ ሲሆን የአወቃቀር ማሻሻያ በማድረግ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን (EEPCo) የሚል ስያሜ ያዘ፡፡ ኮርፖሬሽኑ በ2006 ዓ.ም. እንደገና ወደ ሁለት ተቋማት ተከፍሎ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል (EEP) እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት (EEU) በሚል እንዲደራጅ ተደርጓል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል (EEP) በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 302/2006 እና በተሻሻለው ደንብ ቁጥር 381/2008 መሠረት የሚያከናውናቸው ዝርዝር ተግባራት በዝርዝር ተደንግገዋል፡፡ በመሆኑም ተቋሙ በተሻሻለው በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 381/2008 መሰረት የተቋቋመባቸው ዓላማዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡

  • ከብሔራዊ ግሪድ ጋር የተያያዙ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች፣ ከ66 ኪሎ ቮልት በላይ የሆኑ የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች የግንባታ ሥራዎች የአዋጭነት ጥናት፣ የንድፍ እና የቅየሳ ሥራዎች ማከናወን፣ እንደ አስፈላጊነቱ እነዚህኑ ሥራዎች በኮንሰልታንት ማሠራት፤
  • ከብሔራዊ ግሪድ ጋር የተያያዙ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች፣ ከ66 ኪሎ ቮልት በላይ የሆኑ የማስተላለፊያ መስመሮች እና ማከፋፈያ ጣቢያዎች የግንባታና የማሻሻያ ሥራዎችን ማከናወን፤ እንደአስፈላጊነቱ እነዚህኑ ሥራዎች በሥራ ተቋራጭ ማሠራት፤
  • ከብሔራዊ ግሪድ ጋር የተያያዙ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን፣ ከ66 ኪሎ ቮልት በላይ ኃይል የመሸከም አቅም ያላቸውን የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮችን እና ማከፋፈያ ጣቢያዎችን ማስተዳደር፣ የኦፕሬሽን እና የጥገና ሥራዎችን ማከናወን፤
  • ከ66 ኪሎ ቮልት ደረጃ በላይ በሆኑ መስመሮች የኤሌክትሪክ ኃይልን በጅምላ መሸጥ እና መግዛት፤
  • ከ66 ኪሎ ቮልት በላይ የሆኑ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን ሊዝ ማድረግ፤
  • የሚሸጠውን የኤሌክትሪክ ኃይል በተመለከተ የታሪፍ ማሻሻያ ሀሳብ ማቅረብ፣ ሲፈቀድም ተግባራዊ ማድረግ፤
  • የገንዘብ ሚኒስቴር የሚያወጣውን መመሪያና የፖሊሲ አቅጣጫ መሠረት በማድረግ ቦንድ መሸጥና በዋስትና ማስያዝ እንዲሁም ከሀገር ውስጥና ከውጭ የገንዘብ ምንጮች ጋር የብድር ውል መደራደርና መፈራረም፤
  • ዓላማውን ከግብ ለማድረስ የሚረዱ ሌሎች ተዛማጅ ሥራዎችን ማካሄድ፤

የኤሌክትሪክ አቅርቦት ሥርዓት

በአሁኑ ጊዜ በኃይል መሰረተ ልማት የተገናኙት ማመንጫዎች (ICS) 22 ሲሆኑ በዋነኝነት የውሃ ኃይል ማመንጫ እና የንፋስ ኃይል ማመንጫዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪም ተቋሙ ከደረቅ ቆሻሻ እና ከከርሰ ምድር እንፋሎት ኃይል የሚያመነጩ ጣቢያዎችም አሉት፡፡