ሴቶች ለመልካም ማህበረሰብ ግንባታ ያላቸው ድርሻ ከፍተኛ ነው ተባለ

Published by corporate communication on

ሴቶች በተቋማዊ እና ሀገራዊ ግንባታ ካላቸው ግንባር ቀደም ሚና ባለፈ ለመልካም ማህበረሰብ ግንባታ የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑ ተገለፀ።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የንብረትና አገልግሎት ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ስመኝ አያሌው ዓለም አቀፍ የሴቶችን ቀን ምክንያት አድርገው ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለፁት ሴቶች በልጆች አስተዳደግ እና በቤተሰብ አስተዳደር ያላቸው ችሎታ እና አስተዋይነት ለመልካም ማህበረሰብ ግንባታ ትልቅ ድርሻ አለው።

“ሴቶች በውሳኔ ሰጭነትም ሆነ በተለያዩ ኃላፊነቶች በሴትነታችን ብቻ ሳይሆን በችሎታችን እና በብቃታችን መመረጥ የሚያስችለን አቅም አለን”ያሉት ወ/ሮ ስመኝ ለዚህም ሰፊ እድሎች ሊመቻቹ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሌንሴ ኢደኤ በበኩላቸው የሴቶች ጉዳይ የሰብዓዊነት፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ በመሆኑ ሴቶች ችሎታቸውን በሁሉም ዘርፎች እንዲያጎለብቱ እድል መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።

በተቋሙ ያሉ ብዙዎቹ ሴት ሠራተኞች ባሉባቸው ተደራራቢ ኃላፊነቶች ሙያቸውን እንዳላሳደጉ የገለፁት ኃላፊዋ ይህን ታሳቢ ያደረገ ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልም የዘንድሮውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን (March 8) በምስራቅ ሪጅን ድሬደዋ ከተማ በድምቀት አክብሯል።

 በተያያዘ ዜና የአዳማ 1 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ሠራተኞችም ዓለምአቀፉን የሴቶች ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች አክብረዋል።

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን (March 8) በዓለም 110ኛ እና በአገራችን ደግሞ ለ45ኛ ጊዜ “ሴቶችን የሚያከብር ማህበረሰብ እንገንባ “በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ይገኛል።

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

eighteen − 14 =