ሪጅኑ ባለፉት 6 ወራት ከዕቅዱ በላይ የቅድመ ብልሽት ፍተሻና የጥገና ሥራ አከናወነ

Published by corporate communication on

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የምስራቅ ሪጅን የትራንስሚሽንና ሰብስቴሽን ኦፕሬሽንና ጥገና ቢሮ ባለፉት 6 ወራት የዕቅዱን 102 ነጥብ 38 በመቶ የቅድመ ብልሽት ፍተሻና የጥገና ሥራ ማከናወኑን አስታወቀ፡፡

ቢሮው የስድስት ወር አፈፃፀሙን በጅግጅጋ ሲገመግም ዳይሬክተሩ አቶ ጋሻው እንድሪያስ እንደገለፁት በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን ከዛፍ ንኪኪ የማፅዳት፣ የተሰበሩ ኢንሱሌተሮችን በሌላ የመተካት፣ የመሬት መንሽራተት ምሰሶዎችን እንዳይጎዳ የጋቢዮን ማንጠፍና የተበጠሱ ገመዶችን በሌላ የመተካት ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡

የፖርሲሊን ኢንሱሌተሮችን በፕላስቲክ ኢንሱሌተር የመተካት ስራ መስራቱንም ገልፀዋል፡፡

ይህም የሪጅኑን አፈፃፀም 102 ነጥብ 38 በመቶ አድርሶታል ብለዋል፡፡

ከተመሠረተ ሦስት ወራት ያስቆጠረው የጅግጅጋ ንዑስ ሪጅን የተቋቋመበትን ዓላማ መውጣት እንዲችል ተገቢው ድጋፍ እየተደረገለት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በሪጅኑ ከሪፖርት አቀራረብ፣ የሚሞሉ ዕለታዊ ሎግ ሺቶችን ኦዲት ካለማድረግና ከስልጠና ጋር የተያያዙ የአፈፃፀም ክፍተቶች መታየታቸውን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

አዲሱ የጅግጅጋ ንዑስ ሪጅን በምስራቅ ሪጅን ትራንስሚሽንና ሰብስቴሽን ኦፕሬሽንና ጥገና ቢሮ ስር የተዋቀረና ከሐረር እስከ ጎዴ – ራይቱ ከ700 ኪ.ሜ በላይ ርቀት ያለውን አካባቢ በመሸፍን የጥገናና ኦፕሬሽን ሥራ ለመስራት የተዋቀረ ነው፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

5 × 4 =