ሠራተኞች በአፈፃፀማቸው ልክ ተጠቃሚ የሚሆኑበት አሰራር ተግባራዊ ይደረጋል – የሠው ኃይል ሥራ አስፈፃሚ

በውድድር ጊዜ የትምህርት ዓይነት፣ የትምህርት ደረጃና የስራ ልምድ አያያዝ አግባብነት ባለውና ወጥ በሆነ መልኩ በሁሉም የሥራ ክፍሎች ሊተገበር እንደሚገባ የኢትየጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሰው ኃይል ሥራ አስፈፃሚ አሳሰቡ፡፡
ተቋሙ በቀጣይ ዓላማውን ያማከለና ሠራተኞች ባከናወኑት ተግባር ልክ ተጠቃሚ የሚሆኑበት የውጤት ተኮር ስርዓት ተግባራዊ እንደሚያደርግም ገልፀዋል፡፡
የሠው ሀብት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ተማም አፍደል በበኩላቸው ከማስታወቂያ ጀምሮ የፈተና አወጣጥ፣ የፈተና እርማት እና የውጤት ማሳወቂያ ሂደቶች በተያዘላቸው ስታንዳርድ መሠረት በማጠናቀቅ ከቅሬታ ነፃ የሆነ አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የመሠረታዊ ሠራተኛ ማህበር ሊቀመንበር አቶ መኮንን ክፍሌ ደግሞ በሁሉም የሥራ ክፍሎች ወጥ የሆነ የማወዳደሪያ መስፈርቶችን ከመተግበር አኳያ ክፍተቶች በመኖራቸው ሊስተካከሉ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
በደረጃ ዕድገት፣ በዝውውርና ቅጥር ላይ የሚቀርቡ የሰራተኛ ቅሬታዎች በዘለቄታው ለመፍታት ይረዳ ዘንድ በሠው ኃይል ሥራ አስፈፃሚ የሚወጡ ደንቦችና መመሪያዎች ሳይሸራረፉ በሁሉም የሥራ ክፍሎች ሊተገበሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች እንደገለፁት ለውድድር የሚወጡ ጥያቄዎችን ሚስጥራዊነት እንዲጠበቅ ለማድረግ ራሱን የቻለ የፈተና ቋት መፍጠር ያስፈልጋል፡፡
የሰው ኃይል ሁለንተናዊ አሰራርን የሚያዘምኑ በርካታ ሃሳቦች በተወያዮች የቀረቡ ሲሆን ከመሰል ተቋማት ልምድ በመውሰድ፣ የሚሻሻሉ መመሪያዎችንና ደንቦች በመለየት የተሻለ አሠራርን ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች ማከናወን እንደሚገባም አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
የሰው ኃይል ሥራ አስፈፃሚ እና የመሠረታዊ ሠራተኛ ማህበር አመራሮች የተሳተፉበት ውይይት ላይ በተቋሙ የሚከናወኑ የደረጃ ዕድገት፣ ዝውውር እና የቅጥር ተግባራት ወጥ በሆነና የአሰራር ስርዓትን ባገናዘበ መልኩ እንዲከናወኑ ማድረግ በሚቻልበት መንገድ ላይ ትኩረት አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በአሁኑ ጊዜ ከ8 ሺህ በላይ ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞች አሉት፡፡
0 Comments