ሠራተኛውን ተጠቃሚ የሚያደርግ የብድር ስምምነት ተፈረመ

Published by corporate communication on

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተቋሙን ሠራተኞች ተጠቃሚ የሚያደርግ የብድር  ሥምምነት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በዛሬው ዕለት  ተፈራርሟል፡፡

የመግባቢያ ስምምነቱን  የፈረሙት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አሸብር ባልቻ እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአራዳ ዲስትሪክት የብድር ክፍል ኃላፊ አቶ ቦጋለ ታደሰ  ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አሸብር ባልቻ በፊርማ ሥነ – ሥርዓቱ ላይ  እንደተናገሩት ባንኩ ለአብዛኛዎቹ የኃይል መሰረተልማት ፕሮጀክቶች የፋይናንስ ምንጭ በመሆን የዳበረ የረጅም ዓመታት የሥራ ግንኙነት ተፈጥሯል፡፡

ግንኙነቱን ወደ ሠራተኞችች በማውረድ ሁለቱም ተቋማት የጋራ  ተጠቃሚ የሚሆኑበት የብድር ስምምነት መፈራረማቸው ለዓመታት የዘለቀውን ግንኙነት ይበልጥ ያጠናክረዋል ብለዋል፡፡

ተቋሙ የሚያገኘውን የውጭ ምንዛሪ የሚያስቀምጠውና የሚያንቀሳቅሰው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመሆኑ ስምምነቱ የተቋማቱን ግንኙነት ከማሳደግ ባለፈ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሠራተኞች በሚያገኙት የብድር አገልግሎት ሀብት የሚያፈሩበት ምቹ ሁኔታ ስለሚፈጥር ትብብሩ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው  ዋና ሥራ አስፈጻሚው አሳስበዋል፡፡

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአራዳ ዲስትሪክት የብድር ክፍል ኃላፊ አቶ ቦጋለ ታደሰ  በበኩላቸው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በሀገሪቱ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የገነባ እና እየገነባም የሚገኝ፤ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋርም ለረጅም ዓመታት የዘለቀ ግንኙነት ያለው ግዙፍ ተቋም  መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በተቋሙ ለሚሰሩት ፕሮጀክቶች የፋይናንስ ምንጭ ከመሆን ባለፈ ሠራተኞቹን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች በሚጠቀሙበት ዝቅተኛ የወለድ መጠን ተጠቃሚ የሚሆኑበት የብድር ስምምነት መደረጉ የበለጠ የሚያቀራርበ በመሆኑ መደሰታቸውን አቶ ቦጋለ ገልጸዋል፡፡

በዚህም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለቤት መግዣ፣ ለመኪና መግዣ እና ለግል ጉዳዮች የሚውል የብድር ዓይነቶችን ማቅረቡን የተናገሩት ኃላፊው የድርጅቱ ሠራተኞች በተመቻቸላቸው ዕድል ተጠቃሚ  እንዲሆኑ ጥሪ አቀርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የመሠረታዊ ሠራተኛ መህበር ሊቀ መንበር አቶ መኮንን ክፍሌ እንደተናገሩት የተቋሙ ሠራተኞች በተቋሙ የሥራ ባህርይ የተነሳ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ እንደመሆናቸው ንብረት ለማፍራት ከፍተኛ ቸግር ይገጥማቸው እንደነበር አንስተዋል፡፡

በተለይ በኃይል ማመንጫ የሚሠሩ ሠራተኞች በተለያዩ ምክንያቶች ከኃይል ማመንጫው ሲለቁ ንብረት ስለማይዙ ከፍተኛ ችግር ላይ ይወድቃሉ፡፡

በመሆኑም የዛሬው  የመግባቢያ ሰምምነት ይህን ችግር በመቅፍ በኩል ወሳኝ ሚና እንደ አለው አቶ መኮንን አስረድተዋል፡፡

በዚህም የተቋሙ ማኔጅመንት አባላት በሙሉ ፍላጎት ሠራተኛውን ታሳቢ አድርገው ይህን ውሳኔ ማሳለፋቸውና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ተገቢውን ምላሽ በመስጠቱ በመላው የተቋሙ ሠራተኛ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በፊርማ ሥነ-ስርአቱ ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

11 − one =