ማህበሩ የምክር ቤት አባላት 7ኛ መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ ጀመረ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መሠረታዊ የሠራተኛ ማህበር የምክር ቤት አባላት 7ኛ መደበኛ ጉባኤውን በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ራስ ሆቴል ማካሄድ ጀምሯል፡፡
በጉባኤው መክፈቻ ላይ ከ70 በላይ መሰረታዊ የሠራተኛ ማህበር ያቀፈው የሀገር አቀፍ ኃይል ማመንጫ፣ ኬሚካልና ማዕድን ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ መንገሻ ደሴን ጨምሮ የማህበሩ ሊቀመንበር አቶ መኮንን ክፍሌ እና የማህበሩ የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አባላት ተገኝተዋል፡፡
በጉባኤው ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ መንገሻ ደሴ እንደተናገሩት ፌደሬሸኑ ከአባል ማህበራት በሚቀርብለት የመብት ማስከበር ጥያቄ መሰረት ደረጃውን ጠብቆ፣ የህግ ሥርዓቱን በመከተል የሠራተኛውን መብትና ጥቅም የማስከበር ሥራ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መሠረታዊ የሠራተኛ ማህበር ሥራ አስፈጻሚ የተቋሙ የስራ አመራር ቦርድ አባል በመሆን በተቋሙ ሠላማዊ የሆነ የኢንዱስትሪ ግንኙነት ለማስፈን አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ማህበሩ የሠራተኛውን ጥቅም እና መብት ለማስከበር በሚያደርገው እንቅስቃሴ ለሚያጋጥመው ተግዳሮት ፌደሬሽኑ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ፕሬዝዳንቱ አረጋግጠዋል፡፡
ለ3 ቀናት የሚቆየው የማህበሩ ስብሰባ በኮቪድ -19 በሽታ ህይወታቸውን ላጡ የተቋሙ ሠራተኞች የህሊና ጸሎት በማድረግ እና በተለያዩ ምክንያቶች በተጓደሉ የማህበሩ አባላት ምትክ የተመረጡትን ለአባላቱ የማስተዋወቅ ስነ ስርዓት ተካሂዷል፡፡
ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎው የመሰረታዊ ሠራተኛ ማህበሩ በ2013 በጀት ዓመት ያከናወናቸው ዋና ዋና ተግባራት ሪፖርት፣ የማህበሩ የኦዲት ሪፖርት እና የማህበሩ የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድና በጀት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
0 Comments